የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄዳል

1412

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከማክሰኞ ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄዳል።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም ላይ ውይይት እንደሚያካሂድ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው የጽሁፍ መግለጫ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና የለዉጥ እንቅስቃሴ ሂደት፤ እንዲሁም የድርጅት እና መንግስት የስራ አፈጻጸም ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ  በጥልቀት ተወያይቶ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም በመግለጫው ተገልጿል።

የኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011ዓ.ም በሀዋሳ “አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ማካሄዱ የሚታወስ ነው።

ሀዋሳ ላይ የተካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ ዶክተር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀ መንበር እንዲሁም አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ሊቀ መንበር አድርጎ መርጦም ነበር።

ጉባኤው የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል የሚችልና የዜጎችን የለውጥ ፍላጎት የሚመጥን አመራር በመምረጥ በመጠናቀቁ ስኬታማ እንደሆነም ድርጅቱ መግለጹም ይታወቃል።

በጉባኤው ላይ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫም ድርጅቱ አውጥቷል።

በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል በሚችሉ መሰረታዊ የኅብረተሰቡ ፍላጎቶች ላይ በትጋት ለመስራት በጉባኤው ስምምነት ላይ መድረሱን።

በአሁኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባው ታዲያ በአገሪቷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና እንግልት በዘላቂነት እንዲቆም የሚያደርግ ውሳኔ ይተላለፍበታል ተብሎም ይጠበቃል።

ዜጎች ታግለው ያመጡት ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረውም ስብሰባው በጥልቀት መክሮ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም እንዲሁ።