የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰላምን በማስጠበቅ አገራዊ ለውጡን እናስቀጥላለን አሉ

50

ሀዋሳ ጥር 3/2011 የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰላምን በማስጠበቅ አገራዊ ለውጡን እንደሚያስቀጥሉ ገለጹ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት የአገሪቱን ሰላም ለማስቀጠልና አንድነቷን በማጠናከር ድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የሳይኮሎጂ ተማሪ ቤዛዊት ያደው የአገሪቱን ሰላም ለማስቀጠል ሚናዋን እንደምትጫወት ገልጻለች፡፡

ብሄርን ሳይሆን፤አገራዊ ስሜትን ለማንጸባረቅ እንደምትሰራም ተናግራለች።

ሰላም ለአገር እድገት ያለውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት የኅብረተሰቡን የአብሮነት እሴት በማስፋት ኃላፊነቷን እንደምትወጣም አስታውቃለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የሆርቲካልቸር ተማሪ ሐሰን አያሌው ግጭቶችና አለመግባባቶች በተማሪዎች መካከል መፈጠሩ ተፈጥሯዊ ቢሆንም፤ችግሩን በግጭት ሳይሆን በውይይት መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የአንደኛ ዓመት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ተማሪው ደመቀ ወልዴ በበኩሉ እንደተናገረው ለውጡን ለማስቀጠል ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በመፍጠር ሰላም ለማስፈንና ለውጥ  ለማምጣት እሰራለሁ ብሏል፡፡

ራሱን በሥነ ምግባር በማነፅ  በውይይት የሚያምንና መፍትሄ ፈላጊ ለመሆን እንደሚተጋም ተናግሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ሲሳይ ዮሐንስ እንደገለጸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊነትና ለአገራዊ ለውጡ ወሳኝ ናቸው ፡፡

በዚህም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በክበባት ተደራጅተው በችግሮቻቸው ዙሪያ የሚወያዩበት ዕድል መፈጠሩንና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብሏል፡፡

በውይይት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር  ጥረት እየተደረገ መሆኑንና የሥነ ምግባር ችግር የሚስተዋልባቸውን ተማሪዎችን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም