ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሴራሊዮንን ይጎበኛሉ

54

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሴራሊዮን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ።

አቶ ደመቀ ለጉብኝቱ ወደ ስፍራው ያቀኑ ሲሆን ጉብኝቱ የሚካሄደው የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በጉብኝቱ ወቅት የሴራሊዮንና ኢትዮጵያን ወዳጅነት ሊያጠናክር የሚችል ምክክር የሚደረግ ሲሆን የመግባቢያ ስምምነትም ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።

ሴራሊዮን እ.አ.አ በ1950ዎቹ ከታላቋ ብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ለመውጣት ስታደረግ የነበረውን የነጻነት ትግል ኢትዮጵያ ትደግፍ እንደነበረ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን አገሪቷም እ.አ.አ በ1961 ነጻነቷን አግኝታለች።

ለረጅም ጊዜ የቆየ የፖለቲካ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ሴራሊዮን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1976 ነው።

ሴራሊዮን በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን የከፈተችው እ.አ.አ በ1976 ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞው የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት አርነስት ባይ ኮሮማ በተገኙበት በአዲስ አበባ በአዲስ መልክ ያሰራችውን ኤምባሲ ማስመረቋም ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምታካሄደው በጋና ርዕሰ መዲና አክራ በሚገኘው ኤምባሳዋ በኩል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም