የፕሪሚየር ሊጉ 10ኛ ሳምንት ጨዋታ ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳል

182

አዲስ አበባ ጥር3/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ከመከላከያ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከሶስት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድር ተገናኝተው መከላከያ በቴዎድሮስ ታፈሰ ጎል 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ሩብ ፍጻሜን መቀላቀሉ ይታወሳል።

በክልል ከተሞች በሀዋሳ ከተማ በሜዳው ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ወላይታ ድቻ በሜዳው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን፣ ባህርዳር ከተማ በሜዳው ደደቢትን፣ ስሑል ሽረ በሜዳው ደቡብ ፖሊስን ሲያስተናግዱ በሀዋሳ ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ቡና ጋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ይጫወታሉ።

በ10ኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው ከፋሲል ከተማ ጋር ያደርገው የነበረ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ከነገ በስቲያ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሞሮኮው ሃሳኒያ ዩ ኤስ አጋዲር በሚያደርገው ጨዋታ ምክንያት ለየካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም መራዘሙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡና በ18 ነጥብ ሲመራ፣ ሀዋሳ ከተማ በ17 ነጥብ ሁለተኛ፣ ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ስሑል ሽረ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በሰባት ጎል ሲመራ፣ የአዳማ ከተማዎቹ ዳዋ ሁቴሳና የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በተመሳሳይ ስድስት ግቦች እንዲሁም የሀዋሳ ከተማዎቹ እስራኤል እሸቱና ታፈሰ ሰለሞን በተመሳሳይ አምስት ግቦች ይከተላሉ።