መገናኛ ብዙሃን ለህዳሴ ግድብ በቂ ሽፋን አይሰጡም ተባለ

1742

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 መገናኛ ብዙሃን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚሰጡት ሽፋን በቂ እንዳልሆነ ዲያስፖራዎች ተናገሩ፡፡

ዲያስፖራዎቹ ይህን ያሉት “የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የዲያስፖራው ተሳትፎ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

ተሳታፊዎቹ እንዳሉት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገናኛ ብዙሃን የሚሰጡት ሽፋን ከአገራዊ ፋይዳው አንጻር ውስን ነው።

ከሳዑዲ አረቢያ የመጡት አቶ ከሂረዲን አብዲ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ስለግድቡ ሽፋን ከመስጠት ይልቅ ሌሎች የመዝናኛና ዓለም አቀፋዊ ስፖርታዊ ውድድሮችን በሰፊው ሲዘግቡ ይስተዋላል፡፡

ነገር ግን እንደ ግብፅ ያሉ አገራት መገናኛ ብዙሃን ስለአባይና ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየዕለቱ አዳዲስና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝባቸው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ከእንግሊዝ የመጡት አቶ አለማየሁ ብርሃነ መገናኛ ብዙሃን ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስፋት፣ በጥልቀትና በትኩረት ዘገባዎችን ከመስራት ይልቅ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ ብለዋል፡፡

ይህም ለህዝቡ በተለይም ለወጣቱ ስለ ግድቡ ግንዛቤ በማስረጽ በኩል ውስንነቶች እንዲኖሩ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ከሶማሊላንድ የመጡት አቶ አበበ ኃይለማርያም በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃኑ ስለ ግድቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ፈጥነው የማድረስ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው የሚሉት፡፡

ወላጆች ልጆቻቸው ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩልም መስራት እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል በመድረክ ውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ ዲያስፖራዎች ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ዲያስፖራው እርስ በእርስ ተስማምቶ ለአገሪቱ ህዳሴ በአንድነት መቆም አለበት ያሉት ከአሜሪካ የመጡት ዶክተር ማርታ አባተ ግድቡ  እስከሚጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዘው አቋም የሚያኮራ መሆኑን የተናገሩት ከሳዑዲ አረቢያ የመጡት መምህር ያሲን ራጁም እንዲሁ ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ እስከፍጻሜው እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል፡፡

ነዋሪነታቸውን ኔዘርላንድስ ያደረጉት ወይዘሮ ጽዮን አወቀ በበኩላቸው “ሁሉም በአንድነትና በመተባበር የግድቡን ግንባታ ከዳር ማድረስ የዜግነት ግዴታው ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በዕውቀት፣ በገንዘብና በሞራል ሲደግፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ዓመታት ዲያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ45 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ዘንድሮም 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

“በአሁኑ ወቅት ዋናው ጉዳይ ግድቡን ማጠናቀቅ ነው” ያሉት ወይዘሮ ሮማን፤ ዲያስፖራው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡