ፍርድ ቤቱ የሜቴክ የስራ ኃላፊዎች በተመሰረተባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

47

አዲስ አበባ ጥር 2/2011 ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ /የስራ ኃላፊዎች በተመሰረተባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።

አቃቤ ህግ በቀድሞው የሜቴክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ዛሬ ክስ መስርቷል።

በዚህም መሰረት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በአቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተባቸው ስምንት ግለሰቦች ናቸው።

እነርሱም የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ የሜቴክ የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የግብይትና ሽያጭ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ፣ የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ቸርነት ዳና እና አቶ ረመዳን ሙሳ ናቸው።

በዚሁ መዝገብ ከተከሰሱት ውስጥ ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ፣ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደና እሌኒ ብርሃኑ ያልቀረቡ ሲሆን ፖሊስ ግለሰቦቹን ፈልጎ እንዲያቀርብ ችሎቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ  በንባብ ግልጽ ያደረገ ሲሆን አቃቤ ሕግ 24 የሰው ምስክር፤ 22 የሰነድ ማሰረጃዎችን ማሰባሰቡም ተመልክቷል።

ተከሳሾቹ በሜቴክ ሥር ለሚገኘው የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተሮች ግዥ በተካሔደበት ወቅት፣ ከኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ውጭና ያለጨረታ ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ ወንጀል የተከሰሱ መሆኑ  የዓቃቤ ሕግ ክስ ላይ በዝርዝር ተጠቅሷል።

ከዚህም ሌላ ስልጣንን አለአግባብ በመጠቀምና፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘትና ለሌሎች ለማስገኘት በሚልም ክስ ቀርቦባቸዋል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳቹ የክስ መቃወሚያቸውን በጠበቆቻቸው በኩል  እንዲያቀርቡ ለጥር 17 ቀን 2011ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም