በትግራይ ክልል ባለፉት 6 ወራት 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

876

መቀሌ ጥር 2/2011 በትግራይ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ  መሰብሰቡን የክልሉ ገቢ ለልማት ባለስልጣን አስታወቀ።

በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰው ገቢ የእቅዱን ሙሉ በሙሉ ያሳካ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ18 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፉ ሊላይ ለኢዜአ እንደገለጹት የንግድ ማህበረሰቡ ግብር በወቅቱ መክፈል ለክልሉ ያለውን ፋይዳ እየተገነዘበ መምጣት ለእቅዱ ስኬት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ባለስልጣኑ በሚቀጥሉት ስድስት ወራትም 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመስብሰብ  አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በየአመቱ የሚሰበስበው ገቢ የክልሉን አመታዊ በጀት 43 በመቶ ያህል እንደሚሸፍን ዋና ዳሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በሚደረግ ጥረት በአንዳንድ የእሴት ታክስ ተመዝጋቢዎችና ሸማቾች ላይ የሚታየው ደረሰኝ ያለመስጠትና ያለመጠየቅ ችግር እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለመንግስት ገቢ ማድረግ የሚገባቸውን 15 በመቶ የእሴት ታክስ ክፍያ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ነጋዴዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ግብር ለአገር ግንባታና ልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ለንግድ ማህበረሰብ ግንዛቤ ለመፍጠር  የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በባለስልጣኑ በመቀሌ የቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ገቢ ለልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሃ ተፈሪ ናቸው።

ደረሰኝ የመስጠትና የመጠየቅ ባህል ለማሳደግም እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እያወቁ ህግን የሚተላለፉ አንዳንድ የንግድ ማህበረሰብ አባላትም ህጉን ተፈጻሚ እያደረጉ አለመህናቸውን አቶ ፍሰሀ ገልጸዋል፡፡

በክፍለ ከተማው ባለፉት ስድስት ወራት ደረሰኝ ሳይሰጡ ንብርትና አገልግሎት ሽጠው የተገኙ 21 የንግድ ማህበረሰብ አባላት በነብሰ ወከፍ 50 ሺህ ብር መቀጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሚያገኙት የሽያጭ ገቢ በየወሩ ለመንግስት ገቢ እንደሚያደርጉ የተናገሩት ደግሞ በመቀሌ በንግድ ስራ የተሰማሩ የእሴት ታክስ ተመዝጋቢ አቶ ደስታ ሀይሉ ናቸው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት 15 በመቶ የእሴት ታክስ ጨምረው ከሸጡት እቃ  200 ሺህ ብር ለመንግስት ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስት የእሴት ታክስ ተመዝጋቢዎችና ያልተመዘገቡ በአንድ የጨረታ ሂደት በእኩል ማወዳደር ተገቢ ባለመሆኑ መስተካከል አለበት ብለዋል፡፡

በሆቴል አገልግሎት የተሰማሩ አቶ ይህደጎ ታረቀ በበኩላቸው ከአገልግሎት ሽያጭ 50 ሺህ ብር ያሰባሰቡትን የእሴት ታክስ ጭማሪ ለባለስልጣኑ ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

”ግብር በወቅቱ መክፈል ለመንግስት ሳይሆን ለትውልድ የተስተካከለ መሰረተ ልማት እንዲገነባላቸው ከማሰብ ነው” ብለዋል፡፡