የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድር ሊዘጋጅ ነው

374

አርባምንጭ ጥር 2/2011 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር አገር አቋራጭ ውድድር ሊያዘጋጅ መሆኑን ገለጸ።

ሰሞኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ለሁለት ቀናት ውይይት ሲያደርግ የነበረዉ ማህበሩ የሀገር አቋራጭ ውድድር ለማዘጋጀት መወሰኑን አስታውቋል።

ውድድሩ በመጪዉ ጥር ወር መገባደጃ ላይ በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ የሚካሄድ ሲሆን ዓላማውም የተቀዛቀዘውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ውድድር ለማነቃቃት መሆኑን የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዓባይ በላይሁን ገልጸዋል፡፡

“በተጨማሪም የአቲሌትክስ ስፖርትን በዩኒቨርሲቲዎች ለማሳደግ ብሎም ሌሎች ውድድሮችን ለማካሄድ መሠረት የሚጥል ነዉ” ብለዋል፡፡

በውድድሩ ከ41 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 410 ስፖርተኞችን ለማሳተፍ መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዉድድር ከሁለቱም ፆታ አሸናፊ የሆኑ ሁለት ተማሪዎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችን በመወከል በሐምሌ ወር ጣሊያን በምታዘጋጀው ዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ላይ የሚሳተፉ መሆናቸውንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡