በተጀመረው የቤት ለቤት የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነናል…አስተያየት ሰጭዎች

79
ግንቦት 18/ 2010 በተጀመረው የቤት ለቤት የህክምና አገልግሎት ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ክትትልና በሃኪሞች ድጋፍ ከተስፋ መቁረጥ ህይወት ወጥተው ዳግም  በጤናና በተስፋ መኖር መጀመራቸውን ለረጅም ጊዜ ሳይታከሙ ቤታቸው ለመቀመጥ ተገደው እንደነበር አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽንና የጤና ጣቢያ የህክምና ባለሙያዎችን  ያካተተ የቤት ለቤት የህክምና ቡድን በመዲናዋ ሃያሶስት ጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ለረጅም ጊዜ በልብ ህመም በመሰቃየት በገንዘብ እጥረት ህክምና ሳታገኝ በቤቷ  ውስጥ ለመቆየት መገደዷን የተናገረቸው ወይዘሮ እስከዳር አይታ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና የህክምና ቡድኑ ባደረጉላት ክትትልና ድጋፍ በቤቷና በጤና ተቋም ብሎም በየካቲት 12 ሆስፒታል የተሻለ ህክምና በማግኘቷ አሁን ላይ ጤናዋ የተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም "ስለጤናዬ ግንዛቤ ከማግኘቴ በተጨማሪ  ከአልጋ ተነስቼ እንደማንኛውም ሰው ኑሩዬን እንድኖር የተጀመረው የቤት ለቤት ህክምና አግዞኛል ያለችው ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ ብርቄ ወንድሙ ናት፡፡ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና ሌሎች የህክምና ቡድኖች በቤቷና በጤና ጣቢያ ህክምናና ሌሎች ድጋፎችን  እንድታገኝ መደረጉን  ተከትሎ  ከህመሟ አገግማ ዛሬ በተሻለ ጤና  ላይ ለመገኘት እንዳስቻላት  አስታውቃለች፡፡ ስለቤተሰብ ምጣኔ ምንም አይነት ግንዛቤ ሳይኖራት አራት ልጆች መውለዷን የጠቆመችው  ብርቄ አሁን ላይ  ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች  ባገኘችው ግንዛቤ  የወሊድ መከላከያ መጠቀም መጀመሯንም ተናግራለች፡፡ በጉላሌ ክፍለ ከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ የአይኔአበባ ንጋቱ   በበኩሏ የጤና ግንዛቤ ከመስጠት በተጨማሪ ከቤት መውጣት ላልቻሉ ሰዎች  በቤታቸው የስኳር፣ የደም ግፊትና ሌሎች መሰል በሽታዎች ክትትልና ህክምና  እንዲያገኙና ጤናቸው እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉን አስረድታለች፡፡ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የከተማ ጤና ኤክስቴንሽና የጤና ትምህርት መረጃ ስርጸት    አስተባባሪ አቶ ጌቱ ቢሳ እንደተናገሩት በከተማው ከሁለት አመት በፊት የተጀመረው የጤና ኤክስቴንሽንና የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተ የቤት ለቤት ህክምና ፕሮግራም አሁን ላይ በሃያ ሶስት ጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በፕሮግራሙ በአእምሮና በአካል ጉዳት ችግር ቤተሰቦች የደበቋቸው ሰዎች መገኘታቸውንና ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመው  በከፍተኛ ህመም የሚሰቃዩ ፣አቅመ ደካሞችና ጎዳና ተዳዳሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመት ፕሮግራሙን ወደ አርባ ጤና ተቋማት ለማስፋት በመሰራት ላይ መሆኑን የተናገሩት አስተባባሪው በቀጣይ በሁሉም የጤና ተቋማት ለማስጀመር እቅድ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ከሁለት ሺ ሁለት ዓ.ም ወዲህ በህብረተሰቡና በጤና ተቋማት መካከል ድልድይ በመሆን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛልም ብለዋል፡፡ በፕሮግራሙ የእናቶች በጤና ጣቢያ የመከታተልና የመውለድ ባህል  ወደ ዘጠና ስምንት በመቶ ማሳደግ  የተቻለ ሲሆን የእናቶች ልጆቻቸውን የማስከተብ ሁኔታ ደግሞ መቶ በመቶ መድረሱን  አስረድተዋል፡፡ በከተማዋ እነዚህ ስኬቶች ቢመዘገቡም  የቤቶች አቀማመጥ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ችግሮችና የአመራሩ ትኩረት ማነስ የጤና ኤክስቴንሽን  ውጤቱን ጉራማይሌ አድርጎታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም