በአማራ ክልል ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ጀመረ

85

ባህር ዳርደ/ደሴ/ማርቆስ ጥር 2/2011 በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ኤስ ኤም ኤስ የትራፊክ ህግ መመሪያ ሊተገበር ነው በሚል ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መጀመሩን የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

በደሴ ከተማ የስራ ማቆም አድማ አድርገው የነበሩ  የታክሲ አሽከርካሪዎች ሥራ መጀመራቸው ታውቋል፡፡

የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ውቤ አጥናፉ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት የትራፊክ ህግ መመሪያውን በመቃወም ተቋርጦ የነበረውን የትራንስፖርት አገልግሎት በተደረገ ውይይት ማስጀመር ተችሏል።

ችግሩን ለመፍታትም ከባለሃብቶች፣ ከአስሸከርካሪዎች፣ ከአስሸርካሪ ማህበራትና ከፀጥታ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከባህር ዳር ወደ አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖችና ወረዳዎች ከትናንት ጠዋት ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ከሰዓት በኋላ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል።

ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተቋረጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎትም ስራ መጀመሩን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ከትራፊክ ህግ መመሪያው ጋር በተያያዘ በደሴ ከተማ የታክሲ አሽከርካሪዎች ያደረጉት የስራ ማቆም አድማ በተደረገ ውይይትና በተደረሰ መግባባት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡

ባልተገባ መንገድ የተካሄደው የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጥም ህብረተሰቡን ክፍኛ ያጉላላ ሲሆን በክልሉ የምጣኔ ሀብትና የማህበራዊ  እንቅስቃሴ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደነበረው አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይ የትራንስፖርት መምሪያው በሚተገበርበት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት የሚደረግ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ህብረተሰቡ በውይይት መድረኮች ላይ በመገኘት ለመመሪያው መሻሻል የሚያግዙ ሃሳቦችንም ሆነ ጥያቄዎችን ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተጠቀሱ አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን በትናንትናው ዕለት መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም