እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የፕሪሚየር ሊጉ ተስተተካካይ ጨዋታዎች የሚካሄዱበት ቦታና ቀን ይፋ አደረገ

689

አዲስ አበባ ጥር 2/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች ቦታና ቀን ይፋ አድርጓል።

የፕሪምየር ሊጉ ከጅማሮው አንስቶ በአፍሪካ የክለቦች ውድድርና በሌሎች ምክንያቶች የተራዘሙ ጨዋታዎች እንዳሉበት የሚታወቅ ሲሆን እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ተስተካካይ ጨዋታዎቹ የሚካሄዱበትን ጊዜ እንደሚያሳውቅ ገልጾ ነበር።

በዚሁ መሰረት ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ተከትሎ ክለቡ የማያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ጨምሮ 13 ጨዋታዎች መቼና የት እንደሚካሄዱ አሳውቋል።

በዚሁ መሰረት በሁለተኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ከመከላከያ ሊያደረግ የነበረው ጨዋታ የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም በጅማ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይደረጋል።

በተመሳሳይ በሁለተኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ሊያደረግ የነበረው ጨዋታ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ይከናወናል።  

በሁለተኛ ሳምንት ባህርዳር ከተማ ከስሑል ሽረ ሊደረግ የነበረው ጨዋታ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት እንዲሁም በተመሳሳይ ሁለተኛ ሳምንት የነበረው የአዳማ ከተማና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይደረጋሉ።

በሶስተኛ ሳምንት የነበረው መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከፋሲል ከተማ ጨዋታ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይጫወታል።

በተመሳሳይ በሶስተኛ ሳምንት ሊካሄድ ፕሮግራም ወጥቶለት የነበረው የመከላከያና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይካሄዳል።

በአራተኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርና ድሬዳዋ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ በጅማ ስታዲየም፤ ይከናወናል ተብሏል።

በተመሳሳይ በአራተኛ ሳምንት መካሄድ የነበረበት የደደቢትና መከላከያ ጨዋታ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም  ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይካሄዳል።

በአምስተኛ ሳምንት እንዲደረግ መርሃ ግብር ወጥቶለት የነበረው የመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከባህርዳር ከተማ ጨዋታ የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በስድስተኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርነ ደደቢት ሊያደርጉተ የነበረው ጨዋታ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በጅማ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይከናወናል።

በስምንተኛ ሳምንት ፋሲል ከተማ ከደደቢት የነበረው ጨዋታ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም በጎንደር ስታዲየም፤ በ10ኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ከፋሲል ከተማ ሊያካሄድ የነበረው ጨዋታ ደግሞ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በጅማ ስታዲየም በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይካሄዳል።

በ11ኛ ሳምንት መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከጅማ አባ ጅፋር ሊደረግ የነበረው ጨዋታ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአንደኛው እና ሰባተኛው ሳምንት ውጪ በሌሎቹ የጨዋታ ሳምንታት በተለያዩ ምክንያቶች ለሌላ ጊዜ  ጨዋታዎች ተራዝመዋል።

ገና ከጅምሩ እየተቆራረጠ ወጥነት በሌለው መልኩ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዓመት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ የመርሃ ግብር ማስተካከያዎች በየሳምንቱ መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል።