በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ዳግም መጀመር የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ሊመሰገኑ ይገባል—ዶክተር ደብረጽዮን

888

ሁመራ ጥር 2/2011 የኢትዮጰያና የኤርትራ ህዝቦች ግንኙነት ዳግም እንዲጀመር ያደረጉ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ምስጋና እንደሚገባቸው ዶክተር ደብረጽዮን ገለጹ።

የተጀመረውን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ለማጠናከር በማሰብ የሁለቱ ሃገራት አጎራባች ህዝቦች ዛሬ በሰቲት ሁመራ ተከዜ ወንዝ ድንበር ላይ አክብረዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካሄል እንደተናገሩት የተቋረጠው የሁለቱ ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጀመር ያደረጉት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና ይገባቸዋል።

በኢትዮጰያ የትግራይ ምዕራባዊ ዞንና በኤርትራ ጋሽ ባርካ አጉራባች ህዝቦች ከእንግዲህ የተጀመረውን የሰላም ግንኙነት በማጠናክር ቀጣይ ጉዟቸውን ብሩህ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለግንኙነቱ ዘላቂነትም የትግራይ ክልላዊ አስፈላጊውን ተግባራት ሁሉ እንደሚያከናውንም አስረድተዋል።

የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማው በበኩላችው “የተጀመረ ሰላም ዘላቂ  እንዲሆን  እንሰራለን” ብለዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱና የአካባቢው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነዋሪዎቹ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የጋሽ ባርካ ተወካይና የጉልጅ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሓጎስ ዓምደ ብርሃን ”የተጀመረው ግኑኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሰራለን ከንግዲህ ይህን ሰላም እንጠብቀዋለን ማንም አያቋርጠውም” በለዋል።

የሰቲት ሁመራ ነዋሪ አቶ ይመሰል ከዋኒ እንዳሉት በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም ተረጋግጦ ከወገኖቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸው አስደስቷቸዋል።

“የተጀመረ ሰላም እንዳይቋረጥ ሁለቱም መንግስታት በቅን ልቦና ሊሰሩ ይግባል እኛም የተጀመረውን ሰላም አጠናክርን እንቀጥልበታለን”በማለት ተናግረዋል።

የኦምነ ሓጀር ነዋሪ መሓመድ ብርሃን ዑስማን በበኩላቸው ከ21 አመት በኋላ እንደዚህ ብለን መገናኛታችን ደስ ብሎናል ሰላሙ ቀጣይ እንዲሆንም እንሰራለን ብለዋል።

በተከዜ ወንዝ ዳርቻ በተካሔደው ስነ-ስርዓት ላይ ዶክተር ደብረጽዮንን ጨምሮ የክብር አቀባበል የተደረገላቸው የጋሽ ባርካ ነዋሪዎችና ተወካዮች፣የሃይማኖት አባቶችና፣የምዕራባዊ ትግራይ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።