ብልህ ከሰው፤ ሞኝ ከራሱ…

1023

እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ2010 በተካሄደው የህዝብ ቆጠራ አጠቃላይ ህዝቧ 21 ሚሊዮን 18ሺህ 284 እንደ ነበር ይነገራል፡፡  የሶሪያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰራው ጥናት እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት  ይህ አሃዝ ወደ 18 ሚሊዮን 284 ሺህ 407 ዝቅ ብሏል።  ሀገረ ሶሪያ።

ሶሪያ ከኢሲያ አህጉር  በስተ-ምዕራብ  በኩል የምትገኝ  የአረብ ሀገር ናት። በምዕራብ ሊባኖስና ሜድትራኒያን ባህር፣ በሰሜን ቱርክ፣ በምስራቅ  ኢራቅ፣ በደቡብ ጆርዳን እና በደቡብ ምዕራብ እስራኤል ያዋስኗታል፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2011 የተጀመረው በበሽር አላሳድ መንግስትና በአማፂያን መካከል  የሚደረገው የእርስ በእርስ ጦርነቱ ያስከተለው እልቂት ለህዝብ ቁጥሩ መቀነስ  በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

ለእርስ በእርስ ግጭቱ መነሻም በሀገሪቱ የተንሰራፋው ሙሰኝነት፣ ስራ አጥነት እና የፖለቲካ ነፃነት አለመኖር በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና እየሰፋ ሄዶ ለበርካታ ሶሪያዊያን  እልቂት  ምክንያት ሆኗል ፡፡

በጦርነቱ  ከተሞች ፈራርሰዋል፣ በርካታ ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፣ ከሞት የተረፉትም ህይወታቸውን ለማዳን ቤት ንብረቴን ሳይሉ የተወለዱበትንና ያደጉበትን ቀየ ጥለው ለስደትና ለአገር ውስጥ መፈናቀል ተዳርገዋል፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2018 የተባበሩት መንግስት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው  ሪፖርት እንደሚያመለክተው  የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከ400 ሺህ በላይ ሶሪያዊያንን  ህይወት አሳጥቷል። ከነዚህ ውስጥም 110 ሺህ 613 የሚሆኑት ንፁሃን ዜጎች  ናቸው፡፡

ለሞት ከተዳረጉት ባሻገር 6.1 ሚሊዮን የሚሆኑት በአገር ውስጥ ተፈናቅለዋል፡፡ ወደ 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ሃገራት ተሰደዋል፡፡ በስደት ላይ እያሉ በርካታ ችግሮች ደርሶባቸዋል፡፡ ረሃብና ውሃ ጥም ተፈራርቆባቸዋል፡፡ በጉዞ ላይ እያሉም በርካቶች ላይመለሱ ከዚህ አለም ተሰናብተዋል፡፡ የሰው በድንም እንደ እንስሳ በየሜዳው ወድቆ የአሞራ ሲሳይ ሆኗል፡፡

በሶሪያ መተኪያ የሌለው የበርካታ ሰው ህይወት ጠፍቷል፤ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሷል፡፡ ይህችን አለም እንኳ ገና በውል ያልተገነዘቡና ከእናታቸው ጀርባ ያልወረዱ ጨቅላ ህፃናት የጥይት እራት መሆናቸውም ተስተውሏል።   

በበሽር አላሳድ መንግስት እና በአማፂያኑ መካከል ላለፉት 8 አመታት የተካሄደው  ጦርነት ሶሪያዊያንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፤ በርካታ ሰብዓዊ ጥፋቶች እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም ደርሰዋል፡፡

ሶሪያ የደረሰባት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም እንዲሁ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ጥቂቶችን  እንይ ብንል እንኳ የማህበራዊ አገልገሎት መስጫ ተቋማት እንደ ት/ቤቶች፣ ሆስፒታሎች ፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶች፣ ባንኮች፣ የኤሌክትሪክ መብራቶች፣ ነዳጅ ማደያዎች፣ የንግድ ተቋማት ወዘተ የመሳሰሉት  ይገኙበታል፡፡

ብጥብጡ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአረብ ሊግ ለማደራደር በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ሊሳካ ግን አልቻለም፡፡

እነዚህ ሁለት ተፋላሚ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገርም ሆነ መደራደር እንደምን ተሳናቸው? ህዝብ ጨርሰውስ ማንን ሊመሩ ነው? ጥያቄውን ለነሱ ትቸዋለሁ፡፡

ስለሶሪያ ይህን ያህል ማለቴ ያለምክንያት አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሃገራችን አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶች የማታ-ማታ ከቁጥጥራችን  ውጭ ሆነው የሶሪያ እጣ ፈንታ በኛ ላይ እንዳይደርስ በምሳሌ ለማስገንዘብና ከሶሪያ ምን መማር እንዳለብን ለመጠቆም እንጂ፡፡

ከጦርነት  ደግሞ ምን ትምህርት  ይገኛል እንዳትሉ፡፡ ካላችሁ ደግሞ እኔ ይገኛል ባይ ነኝ፡፡ “ብልህ ከሰው ሞኝ ከራሱ ይማራል”ይላሉ አበው ሲተርቱ፡፡ይህን አባባል አስተውሎ ላየው ለእኛ አገር የሚሰራ ትልቅ እውነት አለው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በአንዳንድ ቡድኖች የሚስተዋሉ ጫፍ የረገጡ አዝማሚያዎች  ልማትን ለማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገምባትና ወደ ፊት እንደ ሃገር አብሮ ለመቀጠል እንደስጋት መታየታቸው አልቀረም ፡፡

አንዳንድ የሀገራችን ፖለቲከኞች ቁጭ ብለው ለመደራደር እርስ በእርስ ይፈራራሉ፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መነቃቀፍን  ይመርጣሉ፡፡ የጋራ አገራዊ አጀንዳ የላቸውም፡፡

እነዚህ አካላት በመጡበት ወይም የኔ ዘውግ ነው በሚሉት ማበረሰብ  እቆረቆርልሃለሁ ወይም እኔ አውቅልሃለሁ  በሚል ሽፋን የግል ጥቅማቸውን ለማጋበስ ላይ ታች የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በምንም አይነት መመዘኛ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሌላቸውን የተዛቡ ትርክቶችን ወደ ማህበረሰቡ በማስረፅ  ህዝቡ እርስ በእርስ እንዲጠራጠርና ወደ ግጭት እንዲገባ ሳይታክቱ  ሲደክሙ የሚውሉም  ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይ ይህ ችግር ጥቂት ተፎካካሪና አክቲቪስት ነን በሚሉ ወገኖች ጎልቶ ይስተዋላል፡፡

ሌላው እንደ ሃገራዊ ስጋት የሚታየው ደግሞ ሚዲያ ነው፡፡ ከተወሰኑ ሚዲያዎች በስተቀር አብዛኛው ሚዲያ አላማውን ስቷል፡፡ ከማስተማር፣ ከማሳወቅና ከማዝናናት ይልቅ አንዱ ሌላውን በመንቀፍ ተጠምዶ ይውላል፡፡ ህዝብን እንደ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር ፋንታ ለማለያየት ሳይደክም ሲሰራ ውሎ ሲሰራ ያድራል፡፡ የፖለቲከኛውን ወይም የጥቂቱን ፍላጎት ብቻ ተሸክሞ ህዝቡን በተስፋ ፈረስ ወደ ፈለገበት አቅጣጫ ሲነዳው ይስተዋላል፡፡

ሌላው መሬት ላይ ያለው የስጋት ምንጭ ደግሞ የሃገር ውስጥ መፈናቀል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እጅግ ቁጥራቸው የበዙ ዜጎቻችን ለሞት፣ለእንግልትና ለስቃይ ተዳርገዋል፡፡ ከቦታ ቦታ እንደልብ ተዘዋውሮ ለመኖርና ሃብት ለማፍራት  የሚንታወቅበት አብሮነትና መቻቻል ቀርቶ ይህ የኔ ነው -ያ- የአንተ ነው አትድረስብኝ አልደርስብህም የሚመስል  እዚያም እዚህም ይስተዋላል።

በአንዳንድ የአገራች አካባቢዎች የሚስተዋለው  ስርዓት አልበኝነትና  እርስ-በእርስ አለመተማመን ካሉን ማህበራዊ እሴቶቻችንና ታሪካዊ ትስስሮቻችን አንፃር ሲታይ ለክፉ ይሰጣል ባይባልም እንኳ  ጥንቃቄ ማድረጉ ግን ይበጃል፡፡

እንደ አንድ ሀገር ለአንድ አላማ ያለመቆም ምልክቶች በጊዜ መፍትሄ ካላገኙ  እንደ ሶሪያ እርስ በእርስ ለመጠፋፋት ምክንያት የማይሆንበት ሁኔታም እንደሌለ ማየቱ ጥሩ ነው።  

በእኔ አስተሳሰብ ይህ ሁሉ የህዝብ ችግር አይደለም፤ በመጣው ለውጥ ምክንያት የግል ጥቅማቸውን የተነጠቁና በእኔ ነኝ የማውቅልህ ካባ ተሸፍነው ተረኛ አግበስባሽና በዝባዥ ለመሆን በሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች እንጂ፡፡

 ታዲያ ምን ተሻለ? የሚሻለውማ  የንግግር ባህልን በማሳደግ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ  መወያየት ነው፡፡ መጀመሪያ ችግሮችን መለየት ቀጥሎ የችግሮቹ ምክንያት ምን እንደሆነ ማወቅና የቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

አንድን የተለየ ወገን  ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ አገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ሃሳቦች ዙሪያ ትኩረት በማድረግ፣ የጋራ ሃገራዊ ግብ ይዞ ለውጤታማነቱ በጋራ መሥራት እና መጠራጠርን አስወግዶ መተማመን ከምንም በላይ ተመራጭ ነው።  

ዜጎቿ የማይሰደዱባት እና የማይፈናቀሉባት፣ እርስ በእርስ የማይገዳደሉባት፣ በኢኮኖሚ የበለፀገችና ለመኖሪያ ምቹ የሆነች  የጋራ ሃገር ለመገንባት እኛው በቀደመው የአብሮነት ባሀላችን በመከባበር፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ መስራት ይጠበቅብናል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ክፉና ደጉንም አብረን አሳልፈናል፤ ወራሪ ጣሊያንን  በተባበረ ክንዳችን ድል አድርገናል፤ ተባብረንም ሀገር መስርተናል፡፡ የተለያዩ የታሪክ ምዕራፎችን ተሸጋግረን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ በነዚህ የታሪክ ምዕራፎች ግን መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡

በተለያዩ  ወቅቶች የተለያዩ አለመግባባቶች ያጋጥሙ ነበር፡፡ አለመግባባቶች ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት ግን ሃገሪቱ ያላትን ማህበራዊ እሴቶች በመጠቀም እልባት ይሰጣቸው ነበር፡፡

በሀገራችን የሚከሰተውን ችግር በዘላቂነት በመፍታት ሙሉ ትኩረትን ወደ ልማት ለማዞር ሁለት ነገሮችን አጣምሮ መጠቀም ግድ ይለናል፡፡

አንደኛው ከላይ የተጠቀሰው ፖለቲከኞች የመወያየትና የመደራደር አቅማቸውን  አሳድገው የጋራ ጉዳዮች ላይ ተባብረው መስራት። ሁለተኛው ደግሞ የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለማስቆም ማህበራዊ  እሴቶቻችንን መጠቀም  ነው፡፡

በተለይ ማህበራዊ እሴቶቻችን በማህበረሰባችን መካከል ለሚከሰቱ ግጭቶች ሁነኛ መፍትሄዎች ናቸው፡፡ ለዚህ አጋዥ የሆኑትን የሃገር ሽማግሌዎች ፣አባ ገዳዎችና  የሃይማኖት አባቶችን  ተሳትፎ  ማጠናከር ግድ ይላል።

እነዚህን ሁለት አማራጮች እና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ሁላችንም ራሳችንን ከስሜታዊነትና ከግጭት በማራቅ  የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል እላለሁ፡፡