በሰሜን ሸዋ ዞን ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን ባለሀብቶች ገለጹ

1011

ፍቼ ጥር 2/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚደረገው ጥረት አበረታች ሆኖ እንዳገኙት ባለሀብቶች ገለጹ፡፡

በዞኑ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ አንዳንድ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በዞኑ ከተሞችና ገጠር ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና ባለሀብቶችን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ባለሀብቱን የሚያነቃቁ ናቸው፡፡

ጽህፈት ቤቱ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድን በማነስ፣የብድር አቅርቦት እንዲፋጠንላቸውና ከቀረጥ ነጻ ደብዳቤ እንዲያገኙ በማድረግ ሥራቸውን እንዳቀላጠፈላቸው አስረድተዋል።

በአስተዳደሩ ከ42 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት አቶ ግሩም አጥናፉ በአስተዳደሩ እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግሥትም የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ የጀመራቸውን የድጋፍና ክትትል ሥራዎች  እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የጀማ ሲሚንቶና ኖራ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኤልሳቤት ወልዱ ፋብሪካቸው ሲሚንቶ፣ ጂብሰምና ለቀለም ፋብሪካ የሚውል ጥሬ ዕቃ በማምረት ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባሉት መዋቅሮች የሚሰጣቸው  ድጋፍ በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ በመሆን ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ  እየደገፈላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ድጋፉ በአካባቢው ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ለዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል። 

የኤሌክትሪክ ኃይል አቀርቦትችግር በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲፈታላቸው ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

በፍቼ ከተማ በኘላስቲክ ውጤቶች ምርት የተሰማሩት አቶ ስለሺ ወርቁ ፋብሪካቸው አገልግሎት የጀመረው ከጥቂት ወራት ወዲህ ቢሆንም በአካባቢው የሚያበረታታ ገበያ በማግኘታቸው ተጨማሪ ማሽነሪዎችን ለመትከል ብድር በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ከባለሀብቱ ጋር የሚያከናውናቸው የመንገድ፣ የውሃና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ባለሀብቱን ከኅብረተሰቡ ጋር የሚያቀራርቡ በመሆናቸው ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደደር ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ በአስተዳደሩ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የተቀላጠፈ አሰራር መዘርጋቱን አመልክተዋል፡፡

አስተዳደሩ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ31 ሚሊየን ብር  በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሦስት ባለሀብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

በዞኑ ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለአገልግሎት የሥራ ዘርፎች ከ1 ሺህ 5ዐዐ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱንም ኃላፊዋ ተናግረዋል።

በዞኑ መሬት ወስደው ያላለሙ 46 ባለሀብቶች 454 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በአስተዳደሩ ከ1999 ጀምሮ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው 302 ፕሮጀክቶች አራት ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡