በተለያዩ መስኮች በተደረጉ ትብብሮች የተጠናከረው የሃገራቱ ግንኙነት

1009

የኢትዮጵያና የአየርላንድ ግንኙነት የጀመረው እኤአ በ1994 ሲሆን በተጠቀሰው አመትም አየርላንድ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷንም መረጃዎች ያመላክታሉ። ኢትዮጵያም እኤአ በ2002  ኤምባሲዋን በደብሊን ልትከፍት ችላለች። በዚህ ጅማሮውን ያደረገው የሁለቱ ሃገራት የትብብር ግንኙነት ተጠናክሮ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ይገኛል።

የሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ከማጠናከር አንፃርም የወቅቱ የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር በሃገራችን ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራችን   ለሶስት ቀናት ይቆያሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካርን ጉብኝት አስመልክቶ ዘ አየሪሽ ኢንዲፔንደንት በዘገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያው አቻቸው አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ጠቅሷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቫራድካር በቆይታቸውም የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የልማት ስራዎች የሚጎበኙ መሆኑንም ዘ አየሪሽ ኢንዲፔንደንት አክሏል።

የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋርም ቆይታ እንደነበራቸው ኢዜአን ጨምሮ ሌሎች የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተከታታይ ዘገባዎቻቸውን አሰራጭተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዊ ተግዳሮቶችን በማለፍ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ለመላው አፍሪካ በምሳሌነት ልትጠቀስ የምትችል ሃገር እንደሆነች ማንሳታቸውን መገናኛ ብዙሃኑ አንስተዋል። 

“ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን ጨምሮ ድህነትንና የተለያዩ ፖለቲካዊ ፈተናዎችን በራሷ አቅም በመፍታት በማደግ ላይ የምትገኝ አገር ናት” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ቫራድካር አክለዋል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ፖለቲካዊ ለውጥ  በምጣኔ ሃብት፣ በኢንቨስትመንትና በፀጥታ ረገድ ከዚህ ቀደም የነበረውን ትብብር በማጠናከር እንደሚሰሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።  

የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር በነበራቸው ውይይት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን የሃገራቱ ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ትኩረቱን አድርጎም እንደነበር ተመልክቷል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በኢትዮጵያ አሁን የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ በበርካታ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ዘርፎች መሻሻል እየታየ መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል ሲሉ ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።። 

ኢትዮጵያ ተለዋጭ አባል ሆና ባገለገለችበት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባል ለመሆን አየርላንድም ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አስመልክተውም ከኢትዮጵያ ልምድ ለመውሰድ መምከራቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ተለዋጭ አባል ሆና ያገለገለችበትን የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤትን በአባልነት ለማገልገል አየርላንድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የዘገበው መረጃው በዚሁ ረገድም ሃገሪቷ ልምድ ለመቅሰም ምክክር መደረጉን አንስቷል። 

ሃያ አምስት አመታትን የተሻገረው የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከዚህ ቀደም በተደረጉ የተለያዩ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነቶችና ትብብሮች ሲዳብር የቆየ ነው።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2014 የአየርላንድ ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሄገንስ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በወቅቱም አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የ136 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ትብብር መፈራረሟንም ማስታወስ ይቻላል።

ፕሬዚዳንት ሊዮ ቫራድካር በትናንተናው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር  በመነጋገር የጀመሩትን ጉብኝት ዛሬ ላሊበላ በመግባት ቀጥለዋል።