በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን ከ20 ዓመታት በላይ የቆዩ የሰራዊት አባላት በክብር ተሸኙ

928

ሽረ እንዳስላሴ ጥር 2/2011 በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን የአገር ዳር ድንበርን ለማስከበር ከ20 ዓመታት በላይ የቆዩ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ትናንት  በክብር ተሸኙ።

አባላቱ ግዳጃቸውን አጠናቅቀው በክብር የተሸኙት በዞኑ የሸራሮ፣ የሽሬ እንዳስላሴና የላእላይ አዲያቦ ወረዳ ነዋሪዎች ነው።

የዞኑ ህዝብም ለሰራዊቱ ያለውን ክብር የሚገልፅ የምስጋና የምስክር ወረቀት በመስጠት ሸኝቷቸዋል።

የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገብረስላሴ ታረቀ  በተደረገው  አሸኛኘት ላይ እንደተናገሩት  አባላቱ የተሰጣቸውን ሕገ መንግሥታዊ ግዳጅ በብቃት ከመወጣት ባለፈ የአካባቢው ህዝብ በሚያካሂዳቸው የልማት ሥራዎች በመሳተፍ ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ተወጥተዋል።

አባላቱ በዞኑ  ህዝብ ውስጥ ምንጊዜም የማይረሳ የግዳጅ አፈፃፀምና የልማት ሥራ ያከናወኑ ጀግኖች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰባተኛ ሜካናይዝድ ዋና አዛዥ ብርጋዲዬር ጄኔራል ጉዑሽ ገብሩ በዚሁ ወቅት ለሰራዊቱ  አባላት በተደረገላቸው የክብር አሸኛኘት ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

ሰራዊቱ ከህዝብ የተፈጠረ፣ ህዝባዊነቱም በተግባር ያስመሰከረና ህዝባዊ ተልዕኮውን በመወጣት ላይ አንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ በመንቀሳቀስም ሕገ መንግሥታዊ ግዳጁን እየፈፀመ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሰራዊቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲረገጋገጥ በመንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ያሉት ደግሞ የአገር ሽማግሌው አቶ ብርሃነ ዓለምሰገድ ናቸው።