የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተሻሽሏል

82

አዲስ አበባ ጥር 2/2011 በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ አንጻራዊ መሻሻል ማሳየቱ ተገለጸ።

በስድስት ወራት ውስጥ ከስድስት ሺህ 500 በላይ ታራሚዎች በምህረት፣ በመደበኛ፣ በአመክሮና በፍርድ ቤት ውሳኔ ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባሶ እንዳሉት፤ "የፍትህ አካላትን ጨምሮ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጸረ-ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሰፈነባቸው ነበሩ"።

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደ ማረሚያ ቤቱ የሚመጡ የቀጠሮ ታራሚዎችና ፍርደኞችን ተቀብሎ ደህንነታቸውን በመጠበቅ ታርመውና ታንጸው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ መዋቅራዊ ለውጥ ተድርጓል ብለዋል።

ቀድሞ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደተገለጸው በማረሚያ ቤቶች ሲደርስ የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት "የስርዓቱ ችግር" እንደነበር ገልጸዋል።

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ይፈጸም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በስድስት ወራት ውስጥ ለውጦች እየታዩበት መሆኑን የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ገለልተኛ የሆኑ የውጭ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ባደረጉት ፍተሻ በማረሚያ ቤቶች የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለውጥ ማሳየቱ ተረጋግጧል።

የማረሚያ ቤቱን አሰራር ለማሻሻል በተደረገ ለውጥ ከ103 በላይ አመራሮች በአዲስ የተተኩ ሲሆን በማረሚያ ቤት አስተዳደር ሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በማረምና በማነጽ ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በቀጣይም በታራሚዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦች መመሪያዎችና አሰራሮች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሸዋ ሮቢትና ዝዋይ ዘመናዊ የማረሚያ ቤቶች እየተገነቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

የማረሚያ ቤት ተቋማቱ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ፣ የተሟላ ህክምና አገልግሎት መስጫ፣ ከአንደኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤት እና የጥበቃ ቦታዎችን የያዙ ናቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ አባ ሳሙኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እየተገነባ ያለው ማረሚያ 96 በመቶ መድረሱን ገልጸው ቀሪ የመሰረተ ልማት ስራ ከተከናወነ በኋላ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ተናግረዋል። 

መንግስት በምርመራ የደረሰባቸው ድብቅ እስር ቤቶችን በተመለከተ እውቅና አላችሁ ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ "ድብቅ እስር ቤቶች ስለመኖራቸው የምናውቀው ነገር የለም እኛም የሰማነው ከሚዲያ ነው" ብለዋል።

የድሬደዋ፣ ዝዋይ፣ ቂሊንጦ፣ ሸዋሮቢት ተሃድሶ ማዕከል፣ የቃሊቲ የሴቶችና ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤቶች በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ስር ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም