በመዲናዋ ፈቃድ ሳይኖራቸው የተሳትፎና የመዝናኛ ስፖርት ውድድር በሚያካሂዱ ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

78

አዲስ አበባ ጥር 1/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ፈቃድ ሳይኖራቸው የተሳትፎና የመዝናኛ ስፖርት ውድድር የሚያካሂዱ አካላት ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ አስታወቀ።

ኮሚቴው ይህን ያለው ከጥር 4 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄዱትን 9ኛው የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ድርጅቶችና የጤና ቡድኖች ልዩ ልዩ የስፖርት ውድድሮችና 8ኛው የሚዲያና የኪነ-ጥበባት ባለሙያዎች የእግር ኳስ ውድድር አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።

በመዲናዋ የተሳትፎና የመዝናኛ ስፖርት ውድድሮች ለሚያካሄዱ ግለሰቦችና ተቋማት ፈቃድ የሚሰጠው የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ ተሰማ ፈቃድ ሳይኖራቸው ውድድር የሚያካሂዱ አካላት መኖራቸውን ኮሚቴ ገልጸዋል።

የሚካሄዱት የውድድር አይነቶች በፉትሳል፣ የጤና ቡድኖችና የመታሰቢያና የሆቴሎች የእግር ኳስ ስፖርቶች ውድድር የሚያካሂዱ አካላት ከኮሚቴው ፈቃድ ሳይወስዱ እንደሚያወዳደሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በደረሰው ጥቆማ ለማወቅ መቻሉን አመልክተዋል።

"እነዚህ አካላት ውድድሩን የሚያዘጋጁት ስፖርቱን ለማሳደግ አስበው ሳይሆን ውድድሩን በማዘጋጀት የሚያገኙትን ገንዘብ ለግል ጥቅም ለማዋል ነው" ሲሉ አቶ ዘነበ ተናግረዋል።

በኮሚቴው በሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮች ላይ የሚያጫውቱ ዳኞች ህጋዊ እውቅና በሌላቸው ውድድር እያጫወቱ መሆኑንም ጥቆማ በመድረሱ ጉዳዩን እያጣራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በመዲናዋ ፈቃድ ሳይኖራቸው የተሳትፎና የመዝናኛ ስፖርት ውድድሮች በሚያካሂዱ ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ህጋዊ ርምጃ እንደሚወሰድም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በውድድሮቹ ላይ የሚያጫውቱት ዳኞች ላይም እድሜ ልክ እገዳ እንደሚጥልም ነው አቶ ዘነበ ያስረዱት።

ከዚህ በፊት በኮቴቤ መምህራን ኮሌጅ ሲካሄድ የቆየ የጤና ቡድኖች ውድድር ከህጋዊነት ጋር በተያያዘ እንዲታገድ መደረጉን አውስተዋል።

ፈቃድ ከኮሚቴው አግኝተው ባዘጋጁት ውድድር ላይ ያገኙትን ገቢ ለኮሚቴው ሪፖርት በማያደርጉ አካላትም ላይ ህጋዊ ፈቃዳቸውን እንደሚነጥቅ አመልክተዋል።

በመዲናዋ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የተሳትፎና የመዝናኛ ስፖርት ውድድሮች የሚያካሂዱ ግለሰቦችና ተቋማት ወደ ህጋዊው መስመር ገብተው ለስፖርቱ እድገትና መስፋፋት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም አቶ ዘነበ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም