በኢሉአባቦር ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት መጠን እየጨመረ ነው

246

መቱ ጥር 1/2011 በቡና ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎች ከኢሉአባቦር ዞን ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት መጠን እያሳደገው መሆኑን የዞኑ ቡና ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ንጉሴ ለኢዜአ እንዳሉት  ከዞኑ 13 ወረዳዎች ባለፉት ስድስት ወራት ከ28 ሺህ 460 ቶን በላይ ደረቅ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል፡፡

በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለገበያ የቀረበው የቡና ምርት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ7 ሺህ 700 ቶን ብልጫ አለው፡፡

የቡና ምርቱን ለገበያ ያቀረቡት በልማቱ የተሳተፉ  590 አርሶ አደሮችና በቡና ንግድ የተሰማሩ 10 ነጋዴዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ለገበያ የሚቀርበው የምርት መጠን ሊያድግ የቻለው  በምርምር የተገኙና የተሻለ ምርት የመስጠት አቅም ያላቸው አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን በማባዛት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ በመቻሉ መሆኑን አቶ አዲሱ አመልክተዋል፡፡

ህገወጥ ግብይትን ለማስቀረትና አርሶአደሩ ምርቱን በጥራት አድርቆ ለገበያ እንዲያቀርብ ትምህርትና ድጋፍ መሰጠቱም ለምርቱ ማደግ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ከተተከሉት  120 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ውስጥ  ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆኑት  በምርምር የተገኙ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከጅማ ምርምር ማዕከል የተገኙ የቡና ዝርያዎች በሄክታር የሚገኘውን የምርት መጠን ከ6 ወደ 12 ኩንታል የሚያሳድጉ ናቸው ተብሏል፡፡

ምርት ሰብሳቢ ነጋዴዎች ምርቱን በህጋዊ መንገድ ብቻ ለገበያ እንዲያቀርቡ እስከ ገጠር ወረዳ ድረስ የቡና ንግድ ህጋዊነትን የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ  መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በመቱ ወረዳ በቡና ንግድ የተሰማሩት አቶ አህመድ ያሲን በቡና ልማት ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ለጥራቱ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ተገቢውን የጥራት ደረጃ ያሟላ ቡና ከአርሶ አደሩ በመረከብ ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸው በዋጋ ላይ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አመልክተዋል፡፡

ምርቱን በህጋዊ መንገድ ለገበያ በማቅረብ ጥራትና መጠኑ እንዲያድግ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ  በቡና ግብይት የተሰማሩ አቶ ሱልጣን አብደላ ሰይድ ናቸው፡፡

” በከተማው የምርት ገበያ ቢኖርና ምርት በቅርበት ማቅረብ ቢችሉ ለገበያ የሚቀርበው ምርት በማሳደግ ረገድ የተሻለ ይሆን ነበር”ብለዋል፡፡

በኢሉአባቦር ዞን በየዓመቱ 60 ሺህ ቶን የቡና ምርት የሚሰበሰብ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 38 ሺህ ቶን  ለገበያ ይቀርባል፡፡

ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመስኩ ተሰማርተው 150 ሺህ ሄክታር  መሬት በቡና ሸፍነው እያለሙ እንደሚገኙ ከዞኑ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡