ፋሲል ከነማ የጥሎ ማለፍ ውድድር መቀላቀሉን አረጋገጠ

95

መቀሌ ጥር 1/2011 ፋሲል ከነማ ወልዋሎ አድግራት ዩኒቨርስቲን  በማሸነፍ ወደ  ቀጣይ ዙር የጥሎ ማለፍ  ውድድር መቀላቀሉን አረጋገጠ፡፡

ቡድኖቹ ዛሬ በትግራይ ስታዲዮም ባከሄዱት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የፋሲል ከነማ ተጨዋች ያሬድ ባየ በ54 ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል፡፡

በዚህም ፋሲል ከነማ በጥሎ ማለፍ ውድድሩ ባስባሰበው 12 ነጥብ ወደ ቀጣይ ዙር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከተቀላቀሉ ስምንት ቡድኖች መካከል አንዱ ሆነዋል፡፡

የፋሲል ከነማ ቡድን መሪ ሀብታሙ ዘዋለ የዋልዋሎ አድግራት ዩኒቨርስቲ ደጋፊዎችና የመቀሌ ነዋሪዎች  ባሳዩት ፍጹም ጨዋነት የተሞላበት ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጨዋታ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባሳዩት መልካም ስነ ምግባር ምስጋናቸውን ያቀረቡት  የቡድን መሪው "ይህም ለሌሎች የፕሪሜር ሊግ ክለቦችም አርአያ የሚሆን ነው" ብለዋል፡፡

" የመቀሌ ህዝብና የወልዋሎ አድግራት ዩኒቨርስቲ ደጋፊዎች  ለሰላምና ለፍቅር የቆመ መሆኑ በተግባር አሳይቶናል፤ እኛም ውለታችን ለመመለስ ዝግጁ ነን " ያለው ደግሞ የፋሲል ከነማ ተጨዋች ሰሎሞን ሀብቴ ነው፡፡

የወልዋሎ  ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ተጨዋች በርሃኑ በጓለ በበኩሉ "ፋሲሎች ጥሩ ተጫውተው አሸንፈውናል" ብሏል፡፡

" ከፋሲል ከነማ ልጆች  አሁን ያሳየነው  ፍቅርና ሰላም ለአንዳች ቀንም እንዲቋረጥ አንፈልግም "ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም