የመከላከያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አጋጥሟቸው የነበረው ችግር መፈታቱ ተገለጸ

63

ሽሬ እንዳስላሴ ጥር 1/2011 የመከላከያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሽሬ እንዳስላሴ ከተማን አቋርጠው ሲልፉ  አጋጥሟቸው የነበረው ችግር መፈታቱን የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገብረስላሴ ታረቀ ለኢዜአ እንደገለጹት ያጋጠመው ችግር የአካባቢው ወጣቶች የሰራዊት ቁሳቁስ ጭነው ከተማውን አቋርጠው በማለፍ ላይ የነበሩ 26 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች (ኦራሎች)  ለማስቆም ሲሉ በተፈጠረው አለመግባባት ነው፡፡

እነዚህ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ መሀል ሀገር ሲንቀሳቀሱ  የከተማዋ ወጣቶች ለማስቆም የተነሳሱት ዞኑን ለማን ትታችሁ ትሄዳላቹ በሚል ስጋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከወጣቶቹ ጋር በተደረገው ውይይት መግባባት ላይ በመደረሱ የተፈጠረው ችግር ተፈትቶ ተሽከርካሪዎቹ  ወደ መሀል ሀገር መንቀሳቀሳቸውን  አቶ ገብረስላሴ አረጋግጠዋል፡፡

የተፈጠረው ችግር በመፍታት በኩል የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አመልክተው ወጣቶቹም ከመከላከያ ሰራዊት ፍቅር እንጂ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለባቸው ገልጸዋል፡፡

ከሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ዳኒኤል ተክሉ በሰጡት አስተያየት  " ለመከላከያ ሰራዊት ያለን ክብር የላቀ ነው ብቻ ሳይሆን የምንመካባቸው ጀግኖች ልጆቻችን ናቸው " ብለዋል።

የኦርቶዶክስ  ኃይማኖት መሪ ንብረእድ  ተስፋዬ ተውልደ በበኩላቸው  የከተማዋ ወጣቶች ከመከላከያ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ጋር የፈጠሩት ጊዚያዊ አለመግባባት መንስኤው የፀጥታ ስጋት ቢሆንም ችግሩ በመግባባት መፈታቱን ተናግረዋል፡፡

" አለመግባባቱ በሰላም መፈታቱ ነው ዋናው ጉዳይ" ያሉት ደግሞ  የእስልምና ኃይማኖት መሪ  ሀጂ እሱሌማን ሲኢድ ናቸው፡፡

የከተማዋ ወጣቶች ተወካይ ወጣት ቢንያም በላይ በበኩሉ "ከመከላከያ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ጋር የተፈጠረው ጊዜያዊ አለመግባበት በሰራዊቱ ያለን ከፍተኛ እምነት የሚሸረሽረው አይደለም" ብለዋል።

ጉዳዩ በሰላም መፈታቱም ደስተኛ እንደሆነም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም