ከማእከሉ የምናገኘውን ምርጥ ዘር በመጠቀም ምርታማነትን አሳድገናል - የአስገደ ፅምብላ ወረዳ አርሶ አደሮች

881
ሽሬ እንዳስላሴ ግንቦት 18/2010 ከሽሬ-ማይፀብሪ እርሻ ምርምር ማእከል ያገኙትን ምርጥ የሩዝና የማሽላ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ መቻላቸውን በትግራይ ሰሜን ምእራብ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የአስገደ ፅምብላ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። የምርምር ማእከሉ እያካሄዳቸው ባሉ የምርምር ስራዎችና ባገኛቸው ውጤቶች ዙሪያ ትናንት በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የአስገደ ፅምብላ ወረዳ  አርሶ አደር አቶ ባሻይ ጣሰው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባለፈው የመኸር ወቅት ከማእከሉ ያገኙትን የማሽላ ምርጥ ዘር በመጠቀም ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳ 43 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውን ገልፀዋል። ያገኙት ምርት ቀደም ሲል የአካባቢ ዘር በመጠቀም ያገኙት ከነበረው 25 ኩንታል ምርት በ13 ኩንታል ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ከምርምር ማእከሉ ባገኙት ምርጥ የሩዝ ዘር ከሸፈኑት ግማሽ  ሄክታር ማሳ ላይ 13 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸው የተናገሩት ደግሞ  በጸለምት ወረዳ  የጻእዳ ቀርኒ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር በላይ እጅጉ ናቸው። አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር በመጠቀም ያገኙት የሩዝ ምርት መጠን ቀደም ሲል የአካባቢ ዘርን በመጠቀም ካገኙ በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ በትግራይ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት የሽሬ-ማይፀብሪ የምርምር ማእከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ደስታ እንዳሉት የምርምር ማእከሉ በአዝርእት፣ በተፈጥሮና በእንስሳት ሃብት፣ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና በቴክኖሎጂ ስርፀት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት አርሶ አደሩን እያገዘ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት በምርምር የተገኙ ‘‘ማይ ፀብሪ አንድና ሁለት‘‘ የተባሉ ምርጥ የሩዝ ዝሪያዎችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ‘‘ብርሃንና ደቀባ ‘‘ የተባሉ ምርጥ የማሽላ ዝርያዎችን ከማግኘት ባለፈ ‘‘ሰቲት አንድና ሁለት የተባሉ የሰሊጥ ዘሮችን በማፍለቅ የአካባቢውን አርሶ አደሮች የውጤቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በተያዘው የመኸር ወቅትም በማእከሉ የተባዙና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሩዝ እና የማሽላ ዝርያዎች በአሁኑ ጊዜ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው፡፡ እስካሁንም ከ50 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአከባቢው አርሶ አደሮች ማከፋፈሉን ተናግረዋል። የምርምር ማእከሉ ከአካባቢው ስነ ምህዳር ጋር የሚስማሙ ምርጥ ዝርያዎችን  አባዝቶ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ለምርታማነት እድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሰሜን ምእራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክላይ ገብረ መድህን ናቸው። ማእከሉ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት አቶ አክላይ እንደገለፁት በተለይ በዞኑ ቀደም ሲል በስፋት የማይመረተውን የሩዝ ሰብል በአርሶ አደሮች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ  እንዲመረት የምርምር  ማእከሉ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። በዞኑ በስፋት የሚገኘውና ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት እየተመናመነ የመጣውን የእጣን ዛፍ መልሶ ማልማት እንዲቻል እየተከናወነ ያለው የምርምር ሥራም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም