ለሀገር ሰላምና ዴሞክራሲያዊ አንድነት መጎልበት የድርሻችንን እንወጣለን ---የጥምረቱ ሊቀመንበር

82

ድሬዳዋ ጥር 1/2011 ለሀገር  ሰላም፣ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት የድርሻቸውን እንደሚወጡ  የኦጋዴን ነጻነት ግንባርና የሶማሌ ነጻነት ጥምረት ሊቀመንበር አድሚራል መሀመድ ኡመር ኡስማን ተናገሩ።

በድሬዳዋና አካባቢው የጥምረቱ  አባላትና ደጋፊዎች ትላንት በከተማው አቀባበል አድርገውለታል።

በአቀባበሉ ስነ ስርዓት ወቅት  አድሚራል መሀመድ  ሁለቱ ድርጅቶች  ጥምረት በመፍጠር ለሶማሌ ህዝብ አንድነትና ሁለንተናዊ ጥቅሞች መረጋገጥ መስራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

" ጥምረቱ የህዝባችን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ለማስቻል ያግዛል "ብለዋል።

በተለይ ለሀገሪቱ  አንደነትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠናከር ሰላማዊ የተቀናጀ እንቅሰቃሴ በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ዓላማ መሳካት የሶማሌ ህዝብ ህብረቱን አጠናክሮ በተቀናጀ መንገድ ለሀገሪቱ ሰላም መረጋገጥ አስተዋጽኦን ለማጎልበት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የታጠቀው ኃይሉ ሙሉ በሙሉ ካምፕ መሆኑንህ የገለጹት ሊቀመንበሩ "መታጠቅና ጫካ መሄድ የሚያስፈልገው የነጻነት መነፈግ፣የመገለልና ባይተዋር የመሆን ጉዳይ ናቸው "ብለዋል፡፡

አሁን በሀገሪቱ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የታጠቀ ኃይል እንደማያስፈልገው አስረድተዋል።

የጥምረቱ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ዘከርያ መሀመድ በበኩላቸው ጥምረቱ ለሶማሌ ህዝብ ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

" በተለይ ወጣቱ በክልሉ ከሚገኘው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ይሰራል " ያሉት ዶክተር ዘከርያ ለዚህ ደግሞ የክልሉና የሀገሪቱ ሰላም መጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳ ተደርጎ በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ አቡበከር አዶሽ ጥምረት የፈጠሩት ድርጅቶች  የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን በመቀበል የትጥቅ ትግሉን በመተው ለሰላም ታላቅ ክብር መስጠታቸው   የሚበረታታ መሆኑን  ገልጸዋል።

የሶማሌ ህዝብ ችግር የሆኑትን ጎሰኝነት፣ድህነት፣ስራ አጥነትና  ጭቆናን በተቀናጀ መንገድ ለማስወገድ የሰላም መንገድ ትልቁ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ዳር ለማድረስ ወጣቱ የመከባበርና የመደማመጥ ባህሉን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።

የሲቲ ዞን ወጣቶች ተወካይ ወጣት ማሀዶ ሙስጠፋ በበኩሉ " ለዓመታት የናፈቅነውን አመራሮቻችንን በአካል በማየታችን ተደስተናል፤ለዚህ ደግሞ ዶክተር አብይ አህመድና መንግስታችንን እናመሰግናለን" ብሏል።

ከጥምረቱ ጎን በመሆን ወጣቱ ለሀገር ሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግሯል፡፡

" ወጣቱ ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር የያዘ የህብረተሰብ ክፍል ነው፤  መንግስትም ሆነ አሁን የመጡት መሪዎቻችን ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል " ያለው ደግሞ ወጣት ነስቲሆ ቃሲም ናት፡፡

ጥምረቱ  በቀጣይም  ህዝባዊ መድረኮች በማዘጋጀት በተለያዩ አካባቢዎች ከደጋፊዎቹ ጋር እንደሚመክር ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም