በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ከግብ ለማድረስ የበኩላችንን እንወጣለን - የጎባ ከተማ ነዋሪዎች

58

ጎባ ጥር 1/2011 የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ከግብ ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጎባ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

የጎባ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፤ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ  የሰላም ኮንፈረንስ ትናንት  ተካሔዷል፡፡

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሌ ሀገረ ስብከት ተወካይ አባ ጥበቡ ቁምላቸው እንደተናገሩት  ቤተክርሲቲያኗ የሕዝቦችን ሰላምና አንድነት ከማስጠበቅ ረገድ ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ ሚና ስትጫወት ቆይታለች፡፡

በአሁኑ ጊዜም ''ቤተክርስቲያኗ የሰላም አምባሳደርነት ተግባሯን በመወጣት  በቤተ እምነቶች  ስለ ሰላም አስፈላጊነትና ጠቀሜታ በልዩ ትኩረት ህዝቡን በማስተማር ላይ ትገኛለች'' ብለዋል ።

''የሰላም ዋጋ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ  በከተማችን ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተከስቶ በነበረው ግጭት ወቅት  መማር ችለናል'' ያሉት ደግሞ ሌላው የኮንፈረንሱ ተሳታፊ  አቶ ኑሬ ሰኢዶ ናቸው፡፡

በሃይማኖትም ሆነ በብሔር በህዝቡ መካከል መከፋፈል ሲፈጥሩ የነበሩ አካላት  የማንኛውንም እምነት የማይወክሉ መሆናቸውንም በተግባር ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል ።

ወጣቶችን በመወከል አስተያየት የሰጠው  መህሙድ ከድር በበኩሉ ''የአገሪቱን ሰላምና ለውጥ የማይፈልጉ ኃይሎች ብዙውን ጊዜ የወጣቶችን የልማት ጥያቄ ወደ ስሜታዊነት በመቀየር ለእኩይ ተግባራቸው ማስፈፀሚያነት ይጠቀሙበታል'' ብለዋል፡፡

''መንግስት   የወጣቶች ብሎም የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በመለየት ደረጃ በደረጃ መልስ መስጠት ይኖርበታል'' ያለው ወጣት መሀሙድ  ወጣቶችም  ከስሜታዊነት ወጥተው በምክንያታዊነት የመመራት እሳቤ እንዲያዳብሩ መልእክት አስተላልፏል  ፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት   የጎባ ከተማ ከንቲባ አቶ አህመድ ሀጂ በበኩላቸው  ለከተማዋም ሆነ  ለአገሪቱ ሰላምና ሁለንተናዊ  ስኬት የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል ።

ከንቲባው እንዳሉት ሰላምን ለማስጠበቅ  በተለይ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በየእምነት ተቋማትና በየአካባቢያቸው ህዝቡን የማወያየትና የማሰተማር ስራን የበለጠ እንዲያጠናክሩት አሳስበዋል ።

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚሁ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ  የእምነት አባቶች፣ የሀገር ሽግሌዎች፣ ወጣቶች፤ ሴቶችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን ለየአካባቢያቸው ሰላም መስፈንም በጋራ ለመስራት ተስማምቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም