የትግራይ ህዝብ ህጋዊ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ ሊረበሽ አይገባም—ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

1646

መቀሌ ታህሳስ 30 /2011 የትግራይ ህዝብ ህጋዊ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ሳይረበሽ በልማቱ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ህጋዊና ኃላፊነቱንም ለመወጣት የሚያስችል ነው።

በመሆኑም የክልሉ ህዝብ ይሄንን ተገንዝቦ ያለምንም መረበሽ የልማት ስራውን በተረጋጋ መልኩ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

ህዝቡ የሚያነሳው የህገ-መንግስት ይከበርልን ጥያቄ እራሱ ከማክበር የሚጀምር መሆኑንም ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር በመግለጫቸው አመልክተዋል።

የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማስከበርን ጉዳይም ህዝቡ በፈጠረው አደረጃጀት አንድነቱን ማስቀጠል እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ባደረጉት የጋራ ስምምነት የሁመራ ኦምሃጀር መንገድ መከፈትም ለሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ጠቃሚ እንደሆነ ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

መንገዱ የሁለቱን ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማሳደግ ባለፈው ቀጣይ ህጋዊ መስመር ለማስያዝም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።