አብዴፓ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አስታወቀ

58

ሰመራ ታህሳስ 30/2011 የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) የአርብቶ አደሩን የልማትና የዴሞክራሲ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አስታወቀ።

የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባር (አርዱፍ) በበኩሉ የክልሉ መሪ ፓርቲ (አብዴፓ) የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች በመደገፍ ከፓርቲው ጋር ተቀራርቦ ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጿል።

የአብዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤለማ አቡበከር እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎች ውስጥ በውጭ ሲንቀሳሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ነው።

ይህም ለውጡ የህብረተሰቡን ፍላጎትና ጥቅም ማዕከል እንዲያደርግ ካለው ጠቀሜታ በተጨማሪ ህብረተሰቡን በየደረጃው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማጎልበት ሚናው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ኤለማ እንዳሉት በውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ የተለያዩ የአፋር ፖለቲካ ደርጅቶች ወደሀገር ውስጥ ገብተዋል።

የፖለቲካ ድርጅቶች የአፋር ህዝብን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ወደሀገራቸውና ክልላቸው ተመልሰው ባላቸው ልምድና እውቀት በተጀመሩ የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎች የበኩላቸውን ሚና ለማበርከት መወሰናቸው እንደሚበረታታ ገልጸዋል።

ይህም አብዴፓ የአርብቶ አደሩን ህዝብ ኑሮ ከመሰረቱ በመለወጥ ሁለንተናዊ ተሳታፊነቱንና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥረለት አስረድተዋል።

ፓርቲው ሀገራዊ ለውጡን ወደክልሉ በማውረድ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የህዝቡ የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብትና በህገ-መንግስቱ የተደነገጉ የዜጎች ሃሳብን ያለገደብ የማንሸራሸር መብት እንዲረጋገጥ ፓርቲው የራሱን ሚና ለመወጣት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

"ለእዚህም የክልሉ መሪ ፓርቲ የአፋር ህዝብ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ ማናቸውም አይነት አማራጭ ካላቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ነው። " ብለዋል።

የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክትል ሊቀመንብር አቶ መሀመድ አወል ወግሪስ በበኩላቸው ፓርቲያቸው ህገ-መንግስቱን አክብሮ በሰላማዊ መንገድ በመታገል ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

"መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶና ግለሰቦች በሃገራችው ፖለቲካ ውስጥ በነጻነት እንዲሳተፉ የጀመረው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተስፋ የሚሰጥ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም ፓርቲያቸው  በክልሉ በተጀመሩ የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሰርአት ግንባታ ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርክት ከክልሉ መሪ ፓርቲ (አብዴፓ) ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም