“የቁጭትና የደስታ እምባ በባሌ ”

1061

መሐመድ ረሻድ ( ከጎባ )

ጎባ ታህሳስ 30/2011 ባሌ ዞን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አስራ ስምንት ዞኖች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ በአገሪቱ በዘርፉ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዞኑ በሚመረተው የስንዴና ሌሎች የሰብል አይነቶች ከራሷም አልፋ አገሪቷ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል የሚታደርገውን ጥረት በማገዝ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል ናት፡፡

 ይሁን እንጂ ዞኑ ካለው እምቅ የልማት አቅም አንፃር ስታይ በተለይ በመንገድ የመሰረተ ልማት ችግር ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ያሳያል፡፡ ዞኑ ከመሃል አገርም ሆነ ከአጎራባች ዞኖች ጋር የሚገናኘው በዙሪያ ጥምጥም መንገድ ነበር ።

የዞኑ ህዝበ ይህንኑ ችግር እንዲፈታለት ለዘመናት ታግሏል ። ለአቤቱታ ያልደረሰበት ቦታም አልነበረም ።ረጅምና እልህ አስጨራሽ ውጣ ውረዶችን ቢጠይቅም አሁን ላይ የብሩህ ተስፋ ጭላንጭል እየታየ ነው ።

ለህዝብ ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ የሚሰጥ መድረክ በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ተዘጋጅቶ ነበር ።   የአካባቢውን ማህበረሰብ ጨምሮ ከፌዴራል እስከ ወረዳው ድረስ የተጋበዙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገለቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡ እኔም እድሉ ገጥሞኝ የዚህ ታሪካዊ መድረክ አካል በመሆኔ እድለኛ አድርጎኛል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ላይ መልስ ያገኘው የትውልዶች ጥያቄ በመሆኑ ነው ፡፡

በፕሮግራሙ ላይ አንድ እንግዳ ነገር አስተዋልኩኝ፡፡  አብዛኛው ማለት በሚቻል ደረጃ የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ በፕሮግራሙ ላይ የታደሙ እንግዶች የከበረ ሰላምታ የሚያቀርቡለት አንድ ሰው ተመለከትኩኝ፡፡ እኔም የዚህን ሰው ማንነት ለማወቅ ጓጓሁኝ፡፡

የተለያዩ ጥያቄዎችም  በውስጤ ይመላለሱ ጀመረ፡፡ እኝህ ሰው ማን ናቸው ?  ለምንስ ነው  አብዛኛውን ሰው ለየት ባለ መልኩ ሰላም የሚላቸው ? ከእለቱ መርሃ ግብር ጋር ያላቸው የተለያ ቁርኝትስ ምንድ ነው ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ተመላለሱብኝ ፡፡

ለጥያቄዎቼ መልስ ፍለጋም ጊዜ አላጠፈሁም፡፡ ከጎኔ የተቀመጡ የአካባቢውን ሰው ስለ ልዩው ሰው  ማንነት መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ ለዚህ መንገድ መጀመርና እውን መሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ አባት መሆናቸውም ተነገረኝ፡፡

የተቀመጡበት ድረስ በመሄድ ሌሎቹ እንዳደረጉት የከበረ ሰላምታዬን በማቅረብ ተዋወቅኩዋቸው፡፡ እሳቸውም ፍቅርና ትህትና የተሞላ ሰላምታ ቸሩኝ – ሐጂ ኢብራሂም በከሩ፡፡

በ90 ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ ፡፡ ውልደታቸውና እድገታቸውም በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ነው፡፡ ትኩር ብሎ ለተመለከተቸው ትናንት ያሳለፉትን የህይወት ውጣ ውረድ በትዝታ ወደ ኋላ ተመልሰው የሚያማትሩ ይመስላሉ፡፡   

ሐጂ ኢብራሂም በባሌ ህዝብ ዘንድ እጅግ የተከበሩና የዞኑን ህዝብ የልማት ጥያቄ ለመንግስት በማቅረብ መንግስትና ህዝብን እንደ ድልድይ በማገናኘት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አባት ስለመሆናቸው ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡

የአካባቢው የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ሼህ አህመድ ከድር ስለ ሐጅ ኢብራሂም ተናግረው አይጠግቡም ። የህዝቡ የመሰረተ ልማት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ የዞኑን ህዝብ በመወከል በተለያዩ ጊዜያት እስከ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ድረስ መዝለቃቸውን ይመሰክራሉ ።

በዞኑ ማህበረሰብ ዘንድ የሚታወሱበት ዋናው የበጎ ተግባር መገለጫቸው ደግሞ “ባሌን ከመሃል ሀገር ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአስፋልት መንገድ ለማገናኘት የሚያስችል የዞኑን ህዝብ ጥያቄ ለማቅረብ ከቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በ2000 ዓ ም የተነጋገሩበት ተጠቃሽ ነው ።

የዞኑን ህዝብ ጥያቄ ለመንግስት የሚያቀርቡበት ሳቢና ትህትና የተሞለበት አካሄዳቸው በብዙዎች ዘንድ ይወደድላቸዋል፡፡

እኔም ሐጂን ኢብራሂም ያኔ ስለ አስፋልት መንገዱ ጥያቄ ያቀረቡበትን ሁኔታ ከአንደበታቸው ለመስማት እድል አግኝቻለሁ ።

  “አባቶቼና ጓደኞቼ ባሌን ከመሃል ሀገር ጋር በተሻለ መንገድ ለማገናኘት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም ። ለጥያቄአቸው መልስ ሳያገኙ በማለፋቸው ግን አደራውን ለኔና ለመሰሎቼ አስተላልፈውት ነበር” በማለት በትዝታ ይተርክሉኝ ጀመር ።

ለያኔው ጠቅላይ ሚኒስቴር ያቀረብኩት ጥያቄ ”እኔም ዕድሜዬ እየገፋ ነው ። ሞት አይቀርምና ከሞትኩኝ ለቀደምት አባቶቼ ስለመንገዱ ጥያቄ ምን ብዬ መልሱን ልነገራቸው?” የሚል ነበር ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጥያቄዬ ጥልቅ መሆኑን በማጤን ” ሞት ለሁሉም የማይቀር ተፈጥሮአዊ ሒደት በመሆኑ እርሶም ጊዜዎት ደርሶ ከጓደኞቿ ጋር ሲገናኙ የባሌ የአስፋልት መንገድ ተሳክቶ ተገንብቷል የሚል የምስራች ይዘው ይሄዳሉ ።  አያስቡ!። አይስጉም! ” የሚል የተስፋ ቃል እንደሰጡዋቸው ያስታውሳሉ ።

ከቃል በዘለለም መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተገንብቶ የዞኑ ህዝብም በተሻለ መንገድ ከመሃል አገር ጋር ለመገናኘት መብቃቱን በሙሉ ደስተኝነት  ተናግረዋል፡፡ 

ባሌን ከአርሲ ዞን ጋር በአጭር ርቀት የሚያገነኘው የ53 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታም የዚሁ አካል ሆኖ ተጀምሯል  ፡፡ ሐጂ ኢብራሂምና ሌሎች የዞኑ ማህበረሰብ አካላትም ለዘመናት ሲያቀርቡት የነበሩት ጥያቄ በመንግስት መልስ በማግኘቱ የግንባታ ማብሰሪያ መርሃ ግብር በህይወት እያሉ በአጋርፋ ከተማ ይፋ ተደርጓል ።

ሐጂ ኢብራሂም በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት መንገዱ ባለመሰራቱ የአካባቢው አርሶ አደሮች የሚያመረጠርቱት የአትክልትና ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶችን ፈጥነው ለገበያ በማቅረብ በሚፈልጉት ዋጋ ለመሸጥ ባለመቻለቸው ለዘመናት የቁጭት እምባ ማፍሰሳቸውን አስታውሰዋል ፡፡

ከአርሲ ዞን ጋር በጋማ ከብቶች በመተገዝ ያለ ድልድይ ለመገናኘት ይደረግ በነበረው ጥረትም በክረምት ወቅት የዋቤ ወንዝ ጨክኖባቸው በደራሽ ውሃ የተወሰዱ ሰዎች ህይወትና በዚህ መንገድ የጠፋውን ንብረት ሲያስታውሱ እንደሚቆጫቸው ነበር የተናገሩት ፡፡ 

“ዛሬ ላይ የትውልድ ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ በህይወት ቆይቼ በማየቴ ዳግም እንደተወለድኩ ነው የምቆጥረው” ብለዋል ሐጂ ኢብራሂም በወቅቱ ባሰሙት ንግግር፡፡

የመንገዱ ግንባታው እውን እንዲሆን የሚፈለግባቸውን ሁሉ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን የሚገልጹት ደግሞ ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር አቶ አብዱረህማን ማህሙድ ናቸው፡፡  የመንገዱ ግንባታ መንግስት የህዝቦችን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ የገባውን ቃል በተግባር ያሳየበት አጋጣሚ  ነው ሲሉም ደስታቸውን ገልፀዋል ።

 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱረህማን በበኩላቸው “የአሊ-አጋርፋ -አርሲ ሮቤ 53 ኪሎ ሜትር አንደኛ ምዕራፍ የመንገድ ፕሮጀክት የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የመንገድ ልማት ዘርፍ ዕቅድ አካል ነው” ሲሉ ገልጸውት ነበር፡፡

መንገዱን ከጠጠር ወደ አስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ለማሳደግ መወሰኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደጉም በላይ በዙሪያ ጥምጥም ይገናኙ የነበረው የአርሲና የባሌ ዞኖችን በአጭር ርቀት እንዲገናኙ መልካም እድል የፈጠረ ነው ተብሏል ፡፡

የሁለቱን ዞኖች ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስርን ይበልጥ ያጠናክራል ፡፡ ለመንገዱ ግንባታም የኢትዮጵያ መንግስት 2 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ፡፡

የግንባታ ሥራውንም በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከሥራ ተቋራጩ ጋር የኮንትራት ውል ስምምነት ተደርሷል ።

ታሪካዊ መንገዱን እንዲገነበ  አደራ የተጣለበት ” ሲሲሲሲ” የተባለ የቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ሥራ ተቋራጭ  ስራ አስኪያጅ ሚስተር ታዎ ኮንት በበኩላቸው ካምፓኒያቸው ባከበተው የረዥም ጊዜ የሥራ ልምድ በመጠቀም የመንገዱን ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በጥራት ሰርቶ እንደሚያስረክብ ቃል ገብተዋል፡፡

ሐጂ ኢብራህም ባለፉት ዓመታት የቁጭት እምባ እንዳነቡ ሁሉ ዛሬ ላይ ደግሞ የደስታ እምባ እንዲያነቡ እድለኛ ያደረጋቸው የአሊ-አጋርፋ-ሮቤ አርሲው መንገድ ግንባታ እውን መሆኑ ብቻ አልነበረም ፡፡

ይልቁንም መንግስት የአካባቢውን የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሮቤ-ጋሰራ እንዲሁም ከጋሰራ-ጊኒር 130 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው  ሌላው የባሌ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ የአስፋልት መንገድ ምላሽ አግኝቶ የግንባታ ስራው በመጀመሩ ጭምር ነው፡፡

 የባሌ ህዝብም ሐጂ ኢብራሂም በከሩ ዘመናትን ለተሻገረ የዓላማ ፅናታቸውና  ለህዝቡ ጥቅም ብለው ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ሰጥቶአቸዋል፡፡

የዞኑን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ  በሰላማዊ መልኩ በማደራጀት በመንግስት ምላሽ እንዲያገኝ ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን አደራ በሚችሉት ሁሉ ታሪክ የሚያስታውሰውን ገድል በመስራት ለአሁኑ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡

ትውልዱም የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ የአባቶቹን አርአያነትና አርቆ አሳቢነትን ባህል በመውረስ ለሰላም ፣ ለልማትና ለአንድነት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል እንለለን፡፡ ሰላም !