አገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ንጽህና አጠባበቅ ተቋማት ቆጠራ ተጀመረ

1289

አዲስ አበባ ታህሳስ 30/2011 በዘመናዊ መንገድ አገር አቀፍ የመጠጥ ውኃ፣ ሳኒቴሽንና ንጽህና አጠባበቅ ተቋማት ቆጠራ መጀመሩን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒቴር ገለጸ።

ቆጠራው የውሃ ተቋማትን ሁለንተናዊ ይዞታ ለማወቅ የሚያግዝና አገልግሎት የማይሰጡ የውሃ ተቋማትን በፍጥነት በመጠገንና ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚያግዝ እንደሆነ ተነግሯል።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው ቆጠራው የሚካሄደው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል።   

በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2030 ዘላቂ ልማት ግቦች የትኩረት መስክ ከሆኑ እቅዶች መካከል የመጠጥ ውኃን ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግቡን ለማሳከት በተለይ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።   

በሁለተኛ የእድገትና ትራስፎሜሽን እቅድ ዘመን በገጠር 25 ሊትር በኪሎ ሜትር በነፍስ ወከፍ በከተማ ደግሞ ከ40 ሊትር እስከ 100 ሊትር በቀን በሰው ተደራሽ ለማደረግ ርብርብ እየተደረገ ነው።   

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ 600 ሺህ የሚገመት የመጠጥ ውኃና የንጽህና ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።   

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በመስኩ የሚሰጠው አገልግሎት ውጤታማነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።      

በአገልግሎት አሰጣጡ ምን ምን ችግሮች በየትኛው አካባቢ እንዳሉ እና በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት በመረጃ ተደግፎ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተቋማት ቆጠራ መጀመሩን አስረድተዋል። 

ሚኒስትሩ ”ቆጠራው በሙከራ ደረጃ  በድሬዳዋና ሀረር ከተሞች ተካሂዷል፤ በዚህኛው ደግሞ በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ነው የተጀመረው” ብለዋል።  

ከዚህ በፊት ከተካሄደው የወረቀት ላይ ቆጠራ በተለየ መልኩ ዘመናዊ ቴክሎጂዎች ተግባራዊ የሚደረጉበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቆጠራውን ለማካሄድ ለ4 ሺህ ቆጣሪዎች እንዲሁም ለ500 አስተባባሪዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን መረጃውን ሰብስቦ ወደ ማዕከል ለመላክ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የታብሌቶች ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል።   

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሶፍትዌር የተጫነባቸው ከ 3 ሺህ 900 በላይ ታብሌቶች ግዥ ከልማት አጋሮች በተገኘ ድጋፍ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።

”አንድ የውኃ ተቋም ምን አይነት ተቋም ነው?፣ የት ይገኛል?፣ ለምን ያህል ሰው አገልግሎት ይሰጣል?፣ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ሲተያይ አንድ ተቋም በምን ያህል ስርጭትና ብቃት ማካሄድ ይችላል? የሚለውን በትክክል ለመለየት ያስችላል” ብለዋል።  

”ቆጠራው የመጠጥ ውኃ ያላገኙ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን በቀላሉ ለመለየት ያስችላል” ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በበጀት አጠቃቀም ላይ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።    

ከዚህ ባለፈም የተቋማት ብልሽት ሲከሰት በፍጥነት ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ቆጠራው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ቆጠራው የተሳካ እንዲሆን ህብረተሰቡና የጸጥታ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ሚኒስትሩ።