የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኞና ማክሰኞ ይደረጋሉ

99
አዲስ አበባ ግንቦት18/2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ሰኞና ማክሰኞ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይደረጋሉ። በዚሁ መሰረት ሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከወላይታ ድቻ እንዲሁም መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በክልል ከተሞች በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ፣ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ፣ በመቐለ ስታዲየም መቐለ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ። በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከጅማ አባ ጅፋር፣ በአርባ ምንጭ ስታዲየም አርባ ምንጭ ከተማ ከወልዲያ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ  የፊታችን ሰኞ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የሚደረጉ ይሆናል፡፡ ማክሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከደደቢት ከቀኑ 11 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 40 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው እንደቅደም ተከተላቸው አንደኛና ሁለተኛ ሲሆኑ፤ መቐለ ከተማ በ39 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ናይጄሪያዊው ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ14 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የኢትዮ ኤሌትሪኩ ጋናዊ አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 10 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም