ሰራዊቱ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመግባት ኅብረተሰቡን እያረጋጋ ነው - የመከላከያ ሚኒስቴር

117

አዲስ አበባ ታህሳስ 30/2011 የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመግባት ኅብረተሰቡን እያረጋጋ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባው  የመከላከያ ሚኒስቴርን የ6 ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል።

የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ እንዳሉት፤ የመከላከያ ሰራዊትን ብቁና ገለልተኛ ለማድረግ ባለፉት 6 ወራት የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጦች ተደርገዋል።

ከነዚህም ተግባራት መካከል የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት አዋጁን ማሻሻል፣ የባህር ሃይል ማደራጀት፣ ሰራዊቱን በህገ መንግስቱ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር ማዋቀር በቅርቡ የተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከኅብረተሰቡና ከአካባቢው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ማረጋጋት ተችሏል ብለዋል።

በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች በማርገብም አንጻራዊ ሰላም አንዲሰፍን ተደርጓል ብለዋል።

በክልሎች አጎራባች ቀበሌዎች በተነሱ የጎሳ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ አድርገናልም ብለዋል ሚኒስትሯ።

የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው "ሰራዊቱ በህገ መንግስቱ መሰረት ብቃትንና የብሄሮችን ተዋጽኦ መሰረት በማድረግ በመደራጀቱ በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶችን ማስቆም ይችላል" ብለዋል።

በዚህም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከክልሎች ፈቃድ ሲያገኝ ፈጥኖ በመግባት የአካባቢው ማህበረሰብ ወደነበረ ሰላሙ እንዲመለስ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመንግስት ይቅርታ አግኝተው ከውጭ የመጡ ነገር ግን ትጥቅ ሳይፈቱ በኅብረተሰቡ መሃል የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በተመለከተም ሰራዊቱ ከክልሎቹ ፈቃድ ካገኘ በቀላሉ ማስቆም እንደሚችል ተናግረዋል።

በሀገሪቷ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊቱ አቅም በላይ እንዳልሆነም ገልጸው፤ "ሰራዊቱ የደህንነት ስራውን ሰርቷል ቀሪው የፖለቲካ ጉዳይ የፖለቲከኞች ነው" ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሰራዊቱ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በመደራጀት የዜጎችን ዘላቂ ጥቅም ማስከበር እንዳለበት አስገንዝቧል።

የመከላከያ ሰራዊት የጀመረው መዋቅራዊ አደረጃጀት መልካም እንደሆነና በቀጣይ አፈጻጸሙ ላይ በጥንቃቄ መስራት እንደሚገባም አመላክቷል።

መከላከያ ሰራዊቱ ውስጣዊ አደረጃጀቱን በሚገባ በመፈተሽ የሰላም ዘብና የሀገር ኩራት መሆኑን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም