በማዕከላዊ ጎንደር ከ1ሺ 500 ለሚበልጡ ተፈናቃዮች ለበዓሉ የምሳ ግብዣ ተደረገ

70

ጎንደር ታህሳስ 29/2011 በነበረ የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው በማዕከላዊ ጎንደር ጊዚያዊ መጠለያ ለሚገኙ ከ1ሺ 500 በላይ ተፈናቃዮች የገናን በዓልን በማስመልከት የምሳ ግብዣ ተደረገላቸው፡፡

የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው  እንደተናገሩት የምሳ ግብዣ የተደረገላቸው በአይምባ በትክል ድንጋይና በሳንጃ ከተሞች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ነው፡፡

በሶስት ጊዚያዊ መጠለያዎች ለሚገኙት ተፈናቃዮች ለተደረገው መስተንግዶ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ 91ሺህ ብር ወጪ አድርጓል፡፡

የመስተንግዶው ዓላማ ተፈናቃዮች በዓሉን በደስታ እንዲሳልፉና፣መንግስትና ህብረተሰቡ ከጎናቸው እንደማይለዩ ለማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከቋራ ወረዳ ተፈናቅሎ በትክል ድንጋይ ከተማ በሚገኘው መጠለያ የሚገኘው ፍቃዱ አማረ መንግስት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ላደረገላቸው መስተንግዶ ምስጋና አቅርቧል፡፡

" ቤት ንብረቴን ጥዬ  በዓሉን በመጠለያ ለማሳለፍ ብገደድም መንግስት በዓሉን በደስታ እንዳሳልፍ ባደረገልኝ መስተንግዶ ተደስቻለሁ "ያሉት ደግሞ ከመተማ አካባቢ የመጡት አቶ ምህረቱ መሰለ ናቸው፡፡

በዓልን ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ከፍተኛ ደስታ የሚሰጥ ቢሆንም በሰላም መደፍረስ ከትውልድ ቀያቸው ቢፈናቀሉም መንግስት በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ መስተንግዶ ማድረጉ ከፍተኛው ደስታ እንደተሰማቸው የተናገሩት ደግሞ  አቶ መሳፍንት ብሩ የተባሉ ተፈናቃይ ናቸው፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር በምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ እንዲሁም በጭልጋና ላይአርማጭሆ ወረዳዎች በተቋቋሙ 10 ጊዚያዊ መጠለያዎች ከ15ሺ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም