በደቡብ ሱዳን ዪኒቲ ግዛት የሚገኙት የነዳጅ ጉድጓዶች በከፊል ማምረት ጀመሩ

49

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2011 በደቡብ ሱዳን ዪኒቲ ግዛት የሚገኙት የነዳጅ ጉድጓዶች ማምረት መጀመራቸውን የአገሪቱ መንግስት አስታወቀ።

በአገሪቱ ላለፉት አምስት ዓመታት በተካሄደው የርእስ በርስ ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ጉድጓዶቹ ማምረት አቁመው ነበር።

ከሰሃራ በታች አፍሪካ ከፍተኛ ድፍድፍ ነዳጅ ክምችት ካላቸው አገራት መካከል በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትጠቀሰው ደቡብ ሱዳን ጦርነት ውስጥ ከመግባቷ በፊት በቀን እስከ 350 ሺህ በርሜል ነዳጅ ታመርት ነበር።  

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ዩኒቱ ግዛት ከሚገኙት16 የነዳጅ ጉድጓዶች መካከል ባለፈው ሳምንት አምስቱ ማምረት መጀመራቸውን የአገሪቱ ነዳጅ ሚኒስትር እስኬይል ጋትኩት መናገራቸውን ብሉምበርግ ጠቅሷል።  

በመጀመሪያው ምእራፍም በቀን 20 ሺህ በርሜል ነዳጅ ለማምረት እቅድ መያዙን አክለዋል። በተያዘው የአውሮፓ ወር ማብቃያ ላይም የምርቱ መጠን በእጥፍ ያድጋል ተብሏል።

የዩኒቱ ግዛት የነዳጅ ጉድጓዶች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ማምረት ከጀመረው የቶማ ሶውዝ የነዳጅ ጉድጓድ ቀጥሎ በደቡብ ሱዳን ነዳጅ ማምረት የጀመረ ሁለተኛው ቦታ ነው።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2013 የተቀሰቀሰውና ላለፉት አምስት ዓመታት የዘለቀው የርስ በእርሰ ጦርነት 400 ሺህ ለሚሆኑ ደቡብ ሱዳናዊያን ህልፈት፣ ለአራት ሚሊዮኖች ደግሞ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

የአገሪቱ ዋነኛ የኃብት ምንጭ የሆነው ነዳጅ ምርት ወደ 130 ሺህ በርሜል በማሽቆልቆሉም ምጣኔ ኃብታዊ ቀውስ አስከትሏል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም