በብሔራዊ ሊጉ ሶዶ ከነማ ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር ባዶ ለባዶ ተለያየ

323

ሰዶ ታህሳስ 29/2011 በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄደው ስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ የወንዶች ብሔራዊ ሊግ ጨዋታ   ሶዶ ከነማ ከአቻው የካ ክፍለ ከተማ  ጋር ባዶ ለባዶ ተለያዩ፡፡

በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሶዶ ከነማ ቡድን ኳስን ተቆጣጥሮ፣አደራጅቶ፣ መሃል የሜዳው ብልጫ ወስዶና የተሻለ የግብ ሙከራዎች በማድረግ  የተሻለ ነበር፡፡

በተረጋጋ መንፈስ መከላከልና የተጋጣሚውን የግብ ዕድል በማጨናገፍ እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት የግብ ክልል በመድረስ ረገድ  ደግሞ የአዲስ አበባው ተወካይ  የካ ክፍለ ከተማ እግር ኳስ ቡድንም ነበር፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ደግሞ ባለሜዳው የሶዶ ከነማ ቡድን ደክሞ የካ ክፍለ ከተማ ጠንክሮ ቀርቦ ነበር፡፡

ኳስን ተቆጣጥሮ  በመጫወት፣ የመሃል ሜዳ ብልጫ በመውሰድና ጨራሽ አጥቂ ባለመያዙ አልተሳካለትም እንጂ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን በመፍጠር የካ  የተሻለ ነበር፡፡

የወላይታ ሶዶ ከነማ ምክትል አሰልጣኝ ሃብታሙ ኃይሌ በሰጡት አስተያየተ ባለፉት ሳምንታት ባደረጉት ጨዋታ ተደጋጋሚ ነጥብ ሲጥሉ መቆየታቸውን አስታውሰው ” በጨዋታው ካሳየነው አቋም አንጻር የተገኘው ነጥብ የሚያስከፋ አይደለም” ብለዋል፡፡

የሜዳ ዕድልንም ለመጠቀም እንዳልቻሉና  ለዚህ ደግሞ ተጋጣሚያቸው  ነጥብ ይዞ ለመመለስ  ይዞ የገባው የጨዋታ ፍልሰት አስተዋጽኦ እንደነበረው  ነው  አሰልጣኝ ሃብታሙ የተናገሩት፡፡

“ጨዋታዉ ለሁለቱም ወሳኝ ከመሆንም በላይ ከተደጋጋሚ ሽንፈት ስለነበረብን ቢቻል ማሸነፍ ካልሆነ ነጥብ  ለመጋራት አቅደን ነበር አሳክተነዋል” ያሉት ደግሞ የየካ ክፍለ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው ናቸው፡፡

በተለይም የሶዶ ከነማ ደጋፊዎች እስከመጨረሻ ሰዓት ድረስ ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ቡድናቸውን ለማበረታታት ሲያሳዩ የነበረው ትዕይንት እንደማረካቸውና ሊቀጥልም እንደሚገባ አሰልጣኝ ባንተይርጋ ተናግረዋል፡፡