በቻይና ዣሚን ከተማ በተደረገ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸነፉ

144

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2011 በቻይና ዣሚን ከተማ በተደረገ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸነፉ።

በውደድሩ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌት ደጀኔ ደበላ እና አትሌት መዲና ደሜ አንደኛ በመውጣት አሸንፈዋል።   

የባለፈው ዓመት የዚህ ውድድር አሸናፊው አትሌት ደጀኔ ደበላ ውድድሩን የጨረሰው በ2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ ጊዜ ነው። 

ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አፈወርቅ መስፍንና ብርሃኑ ነበበው ደግሞ ደጀኔን ተከትለው ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

በተመሳሳይ በሴቶች መካከል የተደረገውን የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መዲና ደሜ  2 ሰዓት 27 ደቂቃ 25 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

አትሌት ሻሾ ኢንሰርሙ እና አትሌት ፋንቱ ጅማ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል።

እንደ አውሮፓዊያ አቆጣጠር ከ2003 ጀምሮ እየተደረገ ባለው የዣሚን የማራቶን ውድድር ባለፉት 10 ተከታታይ ዓመታት በሴቶች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ድልን ተቀናጅተዋል።

በወንዶችም ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያን አትሌቶች በዚህ ውድድር ላይ የበላይነትን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።

በሌላ ዜና ትናንት በጣሊያን ካምፓሲዮ በተደረገ ሀገር አቋራጭ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ሀጎስ ገብረህይወት በቀዳሚነት አጠናቋል።

አትሌት ሀጎስ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 29 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ወስዶበታል።

ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ደግሞ በአራት ሴኮንድ ዘግይቶ በመግባት ሀጎስን ተከትሎ ሁለተኛ ሆኗል። 

ኡጋንዳዊ አትሌት አልበር ጨሙቲ ከአትሌት ሰለሞን ጋር ከፍተኛ ፉክክር ያደረገ ሲሆን በአንድ ሴኮንድ ተቀድሞ ሶስተኛ ሆኗል።

በሴቶች መካከል የተደረገውን የስድስት ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ ቱርካዊቷ አትሌት ያሰሚን ካን  በአሸናፊነት አጠናቃለች።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ስለናት ይስማው ሁለተኛ፣ ኬኒያዊቷ ካሮላይን ቼፕኪሞይ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም