በደሴ የሚገኙ የብአዴን አባል የመንግስት ሰራተኞች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ አካሄዱ

58
ደሴ ግንቦት 18/2010 የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አስተሳብን በመዋጋት  የተገልጋይ እርካታ ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ በደሴ ከተማ የሚገኙ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ አባል የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ፡፡ የድርጅቱ አባል የመንግሥት ሰራተኞች ላለፉት ሁለት ቀናት በደሴ ከተማ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ አካሂደዋል፡፡ ከኮንፍረንሱ ተሳታፊ መካከል አቶ ድልባንተ መካሻው እንደገለፁት በጥልቀ ተሃድሶ ወቅት ከተለዩ በርካታ ችግሮች መካከል የተወሰኑትን መፍታት ቢቻልም በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የህዝቡን ርካታ በሚገባ ከማረጋገጥ አንፃር ውስንነት ይታያል፡፡ በተለይ ስር የሰደደው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ድርጊት የአገልግሎት አሰጣጡ ህዝብ ተኮር እንዳይሆን አድርጎታል። አስተሳሰቡንና ድርጊቱን በመዋጋት የህዝብ ወገንተኛነታቸውን በበለጠ ለማረጋገጥ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። በህዝቦች መካከል አንድነትን የማጠናከር ስራ በትኩረት መከናወን እንደሚገባ ገልፀው በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራኑ አንድነትንና ፍቅርን በመስበክ አገራዊ ህብረት ለመፍጠር መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ በአባላት ዘንድ የአድርባይነት ስሜት በመጎልበቱ በድርጅቱ ቀደም ሲል የነበረው ጠንካራ የመተጋገል መንፈስ እንዳዳከመው  የገለፁት ደግሞ አቶ ደምሴ አበበ ናቸው። በህዝቦች መካከል የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመፍታት ረገድ የድርጅቱ አባላት ጠንክረን ልንሰራ ይገባል'' ብለዋል። የከተማ አስተዳደሩ ብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል መሐመድ በበኩላቸው እንደገለፁት በጥልቅ  ተሀድሶው የተለዩ የከተማ አስተዳደሩ ችግሮች ከህዝቡ ፍላጎትና ችግሩ ካስከተለው ተጽእኖ ስፋት አንጻር አለመፈታቱን ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ስራ አጥነትን፣ የመኖሪያ ቤት ችግርን መቅረፍና በካሳ ክፍያ ዙሪያ የሚስተዋሉ ቅሬታዎችን መፍትሄ ከመስጠት  አንፃር ውስንነቶች መኖራቸውን በተሳታፊዎቹ ተገምግመዋል፡፡ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች በቀጣይ ችግሮቹን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት መግባባት ላይ መድረሳቸውን  አመልክተዋል፡፡ «ጥልቅ ተሃድሶውን በማጥለቅ፣ በማስፋትና ቀጣይነቱን በማረጋገጥ የህዝባችንን ተስፋ እናለምልም'' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው ኮንፍረንስ ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ተጠናቋል፡፡ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ባወጡት መግለጫ አድርባነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የኃይማኖት አክራሪነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም