የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ዉሳኔዎችን አሳለፈ

89

አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2011 የኤፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስር የተለያዩ ስምምነቶች እና የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታሕሳስ 27 ቀን 2011ዓ.ም ባካሄደው 60ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘጋጅተው በቀረቡ የስምምነት ሰነዶች እና የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል፡፡

ምክር ቤቱ በእለቱ የተወያዩባቸው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በህንድ ሪፐብሊክ የተደረገውን የመረጃ እና የመገናኛ ብዙኃን፣  ከኮትድቯር ሪፐብሊክ የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት፣ ከቬንዙዌላ ቦሊቫሪያ ሪፐብሊክ በባህል ዘርፍ ትብብር ለማድረግ፣ ከጋና ሪፖብሊክ በኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን እና በሚዲያ ዘርፍ የተደረገውን ትብብር፣ በሞንተሪያል ፕሮቶኮል ላይ የተደረገውን የኪጋሊ ማሻሻያ ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም በስዊስ የፌዴራል ምክር ቤት በመርሃ ግብር የሚከናወን መደበኛ የአየር አገልግሎቶች ስምምነት፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል የተደረገውን የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ጥበቃ እና የሥራ ስምሪት የመግባቢያ ስምምነቶች ለምክር ቤቱ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም