ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

251

አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የ"እንኳን አደረሳችሁ" መልዕክት ዛሬ አስተላለፉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዛሬ በላከው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ "ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ" ብለዋል።

በዚሁ መልዕክታቸው በቤተ ልሄም የተወለደውን ህጻን ለማየት ከሄዱት ጥበበኞች መካከል ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ "እኛ የእነርሱ ልጆችም ዛሬ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ትኅትናን፣ አብሮነትን እና መከባበርን አስቀድመን መጀመር አለብን" ብለዋል፡፡

"እኛም ከትዕቢት ይልቅ ትኅትናን ገንዘባችን ብናደርግ ወደ ጥላቻ እና ወደ መከፋፈል ከሚወስደው መንገድ ወጥተን በሌላ የፍቅር፣ የመደመር፣ የአብሮነት እና የመተማመን ጎዳና ወደ ከፍታችን እንደምንጓዝ እምነቴ የጸና ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የነገ ተነገ ወዲያ በዓል "‹ሰላማችን ወዴት አለ?› በሚል ጥያቄ ሳይሆን ‹ሰላማችንን አገኘነው" በሚል የማረጋገጫ ቃል እንደሚከበር እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡   

"‹የመጣው እና ይመጣ ዘንድ ያለው ለውጥ በሁላችንም ጥረት የመጣ ነው› ከሚለው የባለቤትነት ስሜት ጀምሮ ‹ለሁላችንም የሚበጅ ነው› እስከሚለው የመተማመን ጫፍ ድረስ ቅን መሆን ብንችል፤ ‹የእገሌ እና የእንቶኔ ለውጥ› ከሚል መጠቋቆም ተላቀን እና እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ለሁላችንም የምትበጅ ኢትዮጵያን እንደምንገነባ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም" ብለዋል፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት፤ "ፈጣሪ አገራችንን የምናሳድግበትንና ራሳችንንም ለታላቅነት የምናበቃበትን ዕድል ሰጥቶናል"

 "እንደ እረኞችና እንደ ሰብአ ሰገል ዐውቀን እንጠቀምበት፡፡ የሚጠበቅብንን አድርገን የሚገባንን እናግኝ፡፡ ታሪክ ማለፉ ላይቀር ወቀሳና ከሰሳን ለትውልድ አናስተላልፍ፤ እኛ በሌሎች እንደተማርነው ሁሉ፣ ሌሎችም ነገ በእኛ መማራቸው አይቀርምና" ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ  "ለዘላለም ትኑር"  ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልካም ምኞት ሙሉ መልዕክት

ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡ የገና በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በከብቶች በረት መወለዱን የምናስብበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ኃይል፣ ሥልጣን፣ ጦርነትና ጭቆና የለመዱት የዚያን ዘመን ሕዝቦች ግን ንጉሥ አድርገው የሚገምቱት በእግሩ ረግጦ፣ በእጁ ጨብጦ፣ በጦሩ ቀጥቅጦ፣ በሰይፉ ቆራርጦ የሚገዛቸውን ነበርና በትኅትና፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም የመጣውን ጌታ ለመቀበል አልቻሉም፡፡

 ክብርና ነጻነትን፣ ሰላምና ፍትሕን፣ ዕድገትና ብልጽግናን በተሳሳተ መንገድ ነበር ሲፈልጉት የነበሩት፡፡ በጦር አንደበትና በፈረስ ጉልበት ነበር ንጉሣቸውን የሚፈልጉት፡፡

የተሳሳተውን መንገድ እንደ ትክክል ስለቆጠሩትና ስለ ለመዱት፣ ትክክለኛው ንጉሥ በትክክለኛው መንገድ ሲመጣ እንግዳ ሆነባቸው፡፡ እንደ ሄሮድስ ያሉት ጦር ናፋቂዎች ለሰላም ጥሪው ሰይፍ መዘዙ፡፡

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ደግሞ ጥቅማችንን፣ ክብራችንንና ሥልጣናችንን እናጣለን ብለው ስለ ሠጉ ፍቅርን በጠብ፣ ይቅርታንም በብጥብጥ ሊያጠፉ ተነሡ፡፡

ከዚያ በፊት በሮማውያን ጭቆና ሲሰቃዩ የነበሩ የጎበዝ አለቆች፣ የመጣላቸውን ሰላም ማጣጣም አቅቷቸው ተሸነፍን በሚል ድርቅታ ደብቀውት የነበረውን ሰይፍና ጎመዳቸውን እንደገና ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡

የቤተልሔም ሕዝብም የክርስቶስ መወለድ በሕይወቱ የሚያመጣለትን ድኅነትና ለውጥ ሊገነዘበው ስላልቻለ በሩን ዘግቶ ተኛ፡፡ ድንግል ማርያምም ልጇን የምትወልድበት ሥፍራ አጣች፡፡

ጥቂት እረኞች ብቻ ነበሩ ነገሩ የገባቸውና፣ እየሆነ በነበረው ነገር በውል የተጠቀሙት፡፡ ወቅቱ እሥራኤላውያን የተከፋፈሉበት ወቅት ነበር፡፡

የሮም ደጋፊና ተቃዋሚ፤ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያንና ኤሴያውያን፤ አይሁዳዊና ሳምራዊ፣ ጸሐፍትና ቀራጮች፣ የሄሮድስና የጲላጦስ፣ ዐርበኛና ባንዳ በሚሉ የመከፋፈያ ጥጋጥጎች እስራኤላውያን እዚህ እና እዚያ ሆነው ይቆራቆሱ ነበር፡፡

ክርስቶስ የተወለደው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም አልቀበለው ያሉት ነገሩን ከየጥቅማቸው አንጻር ብቻ ስላዩት ነው፡፡ እነርሱን ብቻ ካላከበረ፣ ካልጠቀመና ለእነርሱ ብቻ ካልመጣ ብለው እምቢ አሉት፡፡ የእነርሱ ብቻ እንጂ የሌሎችም ጭምር እንዲሆን አልፈለጉትም፡፡

ሰብአ ሰገል ከሩቅ ሀገር ዜናውን ሰምተው ሲመጡ፣ እዚያው ቤተ ልሔም ያሉት ግን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለው በግዴለሽነት ትተውት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ የሮማውያንን ጭቆና፣ የጥንታዊት ሀገራቸውን መፈራረስ፣የታሪካቸውንና የማንነታቸውን መዳከም እያነሡ ይቆጫሉ፣ ይበሳጫሉ፡፡

ነገር ግን የጠፋውን ለመፈለግ፣ የወደቀውን ለማንሣት፣ የደከመውን ለማበርታትና የተሰበረውን ለመጠገን ከመጣው ከክርስቶስ ጋር ለመሆን ግን በፍጹም አልፈለጉም፡፡ ችግሩን ያውቁታል፤ መፍትሔውን ግን ትተውታል፡፡ ተባብረውና ተስማምተው የማያውቁት አይሁድና ሮማውያን እንኳን፣ ክርስቶስን ለመቃወም ሲሉ የጋራ ግንባር ፈጠሩ፡፡

የክርስቶስን ልደት ስናከብር እነዚህን ሁሉ ነገሮች አብረን ልናስባቸው ይገባል፡፡ የክርስቶስ ልደት የልዩነትን ግንብ ያፈረሰ፣ የጠብን ግድግዳ የናደ፣ የጥላቻን መጋረጃ የቀደደ፣ የተዋረዱትን ያከበረ፣ የተለያዩትን አንድ ያደረገ፣ የተበተኑትን የሰበሰበ ነው፡፡

የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ‹እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይለቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ እጅጉን ይልቃል› ተብሎ እንደ ተጻፈው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ይህ ስጦታ ታላቁ ስጦታ ነው፤ በመሆኑም ይህ በዓል የክርስትና አስተምህሮ መሠረት የሆነ ታላቅ በዓል ነው፡፡

አንድ ነገር ታላቅ ስጦታ ስለሆነ ብቻ ሁላችንንም አይጠቅምም፡፡ በቤተ ልሔም ከተማ ከነበሩት እንኳን ብዙዎቹ በክርስቶስ ልደት ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ ልዩነቱ የተፈጠረው ስጦታውን በመቀበልና ባለመቀበል ነው፡፡ አብሮ በመሥራትና ባለመሥራት ነው፤ ዐውቆ በመጠቀምና ባለመጠቀም ነው፡፡

የቤተ ልሔም ሰዎች በከተማቸው የዓለምን ታሪክ የሚለውጥ ተአምር እየተሠራ መሆኑን አልተረዱም፡፡ እንኳን ታሪክ ሊሠሩ ታሪክ ሲሠራ ለማየትም አልፈቀዱም፡፡ ሌሎች ከሩቅ ሀገር ይህንን ታሪክ ለማየትና ለመስማት ሲመጡ ነው የደነገጡት፡፡ ሄሮድስም ራሱን ለመፈተሽ አልፈለገም፡፡

ሥልጣኑን በመሣሪያ ኃይል የሚያስጠብቅ መስሎት የቤተልሔም ሕጻናትን ነው ያስፈጀው፡፡ የሚገርመው ነገር የክርስቶስን መወለድ በቸልታ ያለፉት ግዴለሾቹ የቤተ ልሔም ሰዎች መከራው ግን አልቀረላቸውም፡፡ ሄሮድስ የጨረሰው የእነርሱን ልጆች ነው፡፡

መከራን በመጋፈጥ እንጂ በመተኛት ለማምለጥ አይቻልምና፡፡ ሊቃውንተ አይሁድም ዕውቀታቸውን እየጠቀሱ በመራቀቅ ጊዜውን ያለ ተሳትፎ አሳለፉት፡፡ ከተማሩት ሊቃውንት ይልቅ ያልተማሩት እረኞች ተጠቀሙ፡፡ ዛሬም እንኳን በታሪክ የምናስታውሰው እነርሱኑ ነው፡፡

የተናቁት የቤተልሔም ከብቶች ያደረጉትን አስተዋጽዖ ያህል በዳዊት ከተማ በመኖራቸው በታሪካቸው የሚመጻደቁት ቤተ ልሔማውያን አንዳች ለማድረግ አልቻሉም፡፡ የክርስቶስን መወለድ ስናስብ ሀገራችንንም እናስባት፡፡ በቤተ ልሔምና በዙሪያዋ የነበሩ ሁኔታዎች ዛሬም በሀገራችን አሉ፡፡

ቤተ ልሔማውያን በእጃቸው ያገኙትን ጸጋ መጠቀም አልቻሉም፤ በቅናት፣ በግዴለሽነት፣ በጥቅም ሽኩቻ፣ በየወገኑ በመከፋፈልና በሥልጣን ጥም ተነክረው ዕድላቸውን አባከኑት፡፡ እኛም በዘመናችን ያገኘነውን ሀገራችንን የመለወጥ፣ የማሻሻል፣ የማሳደግና የማዘመን ዕድል እንዳናጣው እንደ ልባም ሰው ማሰብ አለብን፡፡ እንደ ቤተ ልሔማውያን በቅናት ተቃጥለን፣ በግዴለሽነት ተኝተን፣በጥቅምና በሽኩቻ ተባልተን፣ በመከፋፈል ተበታትነን፣በሥልጣን ጥም ሰክረን ያገኘነውን ዕድል ከእጃችን ላይ እንዳንጥለው የምናስብበት ጊዜ ላይ ነን፡፡

ክርስቶስ ሁሉን ነገር ትቶ በረት ላይ እንዲተኛ ያደረገው ለእኛ ለወገኖቹ ያለው ፍቅር ነው፡፡ የሚያሰልፈው የመላእክት ሠራዊት አጥቶ አይደለም፤ በመብረቅ ማጥፋት፣ በንፍር መምታት ተስኖትም አይደለም፡፡ ፍቅር ያድናል፣ ይቅርታ ይጠግናል ብሎ እንጂ፡፡ ወገናችንን በእውነት የምንወድ ከሆነ ሰላምን እንጂ ሰይፍን ለምን እናስቀድማለን? ፍቅርን እንጂ ጠብን ለምን እንሰብካለን? አንድነትን እንጂ መለያየትን ለምን እናመርታለን? ይቅርታን እንጂ ጥላቻን ለምን እንተክላለን? ይህ በዓልኮ ሰውና መላእክት፣ ፍጡርና ፈጣሪ፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሰማይና ምድር አንድ የሆኑበት በዓል ነው፡፡

መለያየትንና መጠፋፋትን እየዘራን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ‹ሰላም በምድር ይሁን› የተባለበት ነው፡፡ የጦርነትን ዘገር እየነቀነቅን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ እረኞችና ከብቶች መጠለያ ያጣውን ጌታ ያስጠለሉበት በዓል ነው፡፡ ታድያ ዛሬ ሂድ፣… ውጣ፣…. ልቀቅ፣…. እያልን የገዛ ወገናችንን እያሳደድን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ለወገን ጥቅም ሲሉ ራስን የመስጠት በዓል ነው፡፡

ለራሳችን ጥቅም ስንል ወገኖቻችንን እያጋደልን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ሰውና መላእክት አንድ ሆነው የሰላም መዝሙር የዘመሩበት ድንቅ በአል ነው፡፡ ተለያይተን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰምን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ሰብኣ ሰገል የተወለደውን ሕጻን ለማግኘት ከሄዱበት ዐውድ ብዙውን ነገር ቀይረው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን መጽሐፍ ይናገራል፡፡

እኒያ የጥበብ ሰዎች የሰላሙን ንጉሥ ካገኙት በኋላ በሌላ መንገድ - በሌላ ኃይለ ቃል እና በሌላ እምነት የመልስ ጉዟቸውን አድርገዋል፡፡ ሲሄዱ በሄሮድስ ቤተ መንግሥት በኩል ቢሆንም ሲመለሱ ግን ጎዳናቸውን ቀይረዋል፤ ሲመጡ ‹የአይሁድ ንጉሥ የት ነው?› እያሉ ቢፈልጉትም አግኝተውት ሲመለሱ ግን ‹የዓለማት ንጉሥ› ብለው ተናግረዋል፡፡

‹ወዴት አለ?› ብለው እየፈለጉት መጥተው ነበር፡፡ አግኝተውት ሲመለሱ ግን‹ አገኘነው› ብለው ተደስተዋል፡፡ ከእነዚያ የጥበብ መንገደኞች መካከል ኢትዮጵያውያን ዋኖቻችንም ነበሩበት፡፡ እኛ የእነርሱ ልጆችም ዛሬ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ትኅትናን፣ አብሮነትን እና መከባበርን አስቀድመን መጀመር አለብን፡፡

እንዲያ ከሆነ የነገ ተነገ ወዲያ በዓሎቻችንን ‹ሰላማችን ወዴት አለ?› በሚል ጥያቄ ሳይሆን ‹ሰላማችንን አገኘነው‹ በሚል የማረጋገጫ ቃል እንደምናከብር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እኛም ከትዕቢት ይልቅ ትኅትናን ገንዘባችን ብናደርግ ወደ ጥላቻ እና ወደ መከፋፈል ከሚወስደው መንገድ ወጥተን በሌላ የፍቅር፣ የመደመር፣ የአብሮነት እና የመተማመን ጎዳና ወደ ከፍታችን እንደምንጓዝ እምነቴ የጸና ነው፡፡

‹የመጣው እና ይመጣ ዘንድ ያለው ለውጥ በሁላችንም ጥረት የመጣ ነው› ከሚለው የባለቤትነት ስሜት ጀምሮ ‹ለሁላችንም የሚበጅ ነው› እስከሚለው የመተማመን ጫፍ ድረስ ቅን መሆን ብንችል፤ ‹የእገሌ እና የእንቶኔ ለውጥ› ከሚል መጠቋቆም ተላቀን እና እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ለሁላችንም የምትበጅ ኢትዮጵያን እንደምንገነባ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡

ፈጣሪ ሀገራችንን የምናሳድግበትንና ራሳችንንም ለታላቅነት የምናበቃበትን ዕድል ሰጥቶናል፡፡ እንደ ቤተ ልሔም ሰዎች ስንዘናጋ፣ እንደ ሄሮድስ ሾተል ስንሞርድ፣ እንደ ሊቃውንተ አይሁድ በትንሽ በትልቁ ስንጨቃጨቅ፣ እንደ ዘመኑ ሰዎች ስንከፋፈል፣ እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሥልጣንና ጥቅም ቀረብን ብለን በኩርፊያ ስናምጽ፣ ዕድሉ እንዳያልፈን፡፡

እንደ እረኞችና እንደ ሰብአ ሰገል ዐውቀን እንጠቀምበት፡፡ የሚጠበቅብንን አድርገን የሚገባንን እናግኝ፡፡ ታሪክ ማለፉ ላይቀር ወቀሳና ከሰሳን ለትውልድ አናስተላልፍ፤ እኛ በሌሎች እንደተማርነው ሁሉ፣ ሌሎችም ነገ በእኛ መማራቸው አይቀርምና፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! መልካም በዓል አመሰግናለሁ፡፡ ታኅሳስ 28፣ 2011 ዓ.ም

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አሕመድ፣ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ያስተላለፉት መልዕክት ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ የገና በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በከብቶች በረት መወለዱን የምናስብበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ኃይል፣ ሥልጣን፣ ጦርነትና ጭቆና የለመዱት የዚያን ዘመን ሕዝቦች ግን ንጉሥ አድርገው የሚገምቱት በእግሩ ረግጦ፣ በእጁ ጨብጦ፣ በጦሩ ቀጥቅጦ፣ በሰይፉ ቆራርጦ የሚገዛቸውን ነበርና በትኅትና፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም የመጣውን ጌታ ለመቀበል አልቻሉም፡፡

ክብርና ነጻነትን፣ ሰላምና ፍትሕን፣ ዕድገትና ብልጽግናን በተሳሳተ መንገድ ነበር ሲፈልጉት የነበሩት፡፡ በጦር አንደበትና በፈረስ ጉልበት ነበር ንጉሣቸውን የሚፈልጉት፡፡ የተሳሳተውን መንገድ እንደ ትክክል ስለቆጠሩትና ስለ ለመዱት፣ ትክክለኛው ንጉሥ በትክክለኛው መንገድ ሲመጣ እንግዳ ሆነባቸው፡፡ እንደ ሄሮድስ ያሉት ጦር ናፋቂዎች ለሰላም ጥሪው ሰይፍ መዘዙ፡፡

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ደግሞ ጥቅማችንን፣ ክብራችንንና ሥልጣናችንን እናጣለን ብለው ስለ ሠጉ ፍቅርን በጠብ፣ ይቅርታንም በብጥብጥ ሊያጠፉ ተነሡ፡፡ ከዚያ በፊት በሮማውያን ጭቆና ሲሰቃዩ የነበሩ የጎበዝ አለቆች፣ የመጣላቸውን ሰላም ማጣጣም አቅቷቸው ተሸነፈን በሚል ድርቅታ ደብቀውት የነበረውን ሰይፍና ጎመዳቸውን እንደገና ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡

የቤተ ልሔም ሕዝብም የክርስቶስ መወለድ በሕይወቱ የሚያመጣለትን ድኅነትና ለውጥ ሊገነዘበው ስላልቻለ በሩን ዘግቶ ተኛ፡፡ ድንግል ማርያምም ልጇን የምትወልድበት ሥፍራ አጣች፡፡ ጥቂት እረኞች ብቻ ነበሩ ነገሩ የገባቸውና፣ እየሆነ በነበረው ነገር በውል የተጠቀሙት፡፡

ወቅቱ እሥራኤላውያን የተከፋፈሉበት ወቅት ነበር፡፡ የሮም ደጋፊና ተቃዋሚ፤ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያንና ኤሴያውያን፤ አይሁዳዊና ሳምራዊ፣ ጸሐፍትና ቀራጮች፣ የሄሮድስና የጲላጦስ፣ ዐርበኛና ባንዳ በሚሉ የመከፋፈያ ጥጋጥጎች እስራኤላውያን እዚህ እና እዚያ ሆነው ይቆራቆሱ ነበር፡፡

ክርስቶስ የተወለደው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም አልቀበለው ያሉት ነገሩን ከየጥቅማቸው አንጻር ብቻ ስላዩት ነው፡፡ እነርሱን ብቻ ካላከበረ፣ ካልጠቀመና ለእነርሱ ብቻ ካልመጣ ብለው እምቢ አሉት፡፡ የእነርሱ ብቻ እንጂ የሌሎችም ጭምር እንዲሆን አልፈለጉትም፡፡ ሰብአ ሰገል ከሩቅ ሀገር ዜናውን ሰምተው ሲመጡ፣ እዚያው ቤተ ልሔም ያሉት ግን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለው በግዴለሽነት ትተውት ነበር፡፡ የሮማውያንን ጭቆና፣ የጥንታዊት ሀገራቸውን መፈራረስ፣የታሪካቸውንና የማንነታቸውን መዳከም እያነሡ ይቆጫሉ፣ ይበሳጫሉ፡፡ ነገር ግን የጠፋውን ለመፈለግ፣ የወደቀውን ለማንሣት፣ የደከመውን ለማበርታትና የተሰበረውን ለመጠገን ከመጣው ከክርስቶስ ጋር ለመሆን ግን በፍጹም አልፈለጉም፡፡

ችግሩን ያውቁታል፤ መፍትሔውን ግን ትተውታል፡፡ ተባብረውና ተስማምተው የማያውቁት አይሁድና ሮማውያን እንኳን፣ ክርስቶስን ለመቃወም ሲሉ የጋራ ግንባር ፈጠሩ፡፡ የክርስቶስን ልደት ስናከብር እነዚህን ሁሉ ነገሮች አብረን ልናስባቸው ይገባል፡፡ የክርስቶስ ልደት የልዩነትን ግንብ ያፈረሰ፣ የጠብን ግድግዳ የናደ፣ የጥላቻን መጋረጃ የቀደደ፣ የተዋረዱትን ያከበረ፣ የተለያዩትን አንድ ያደረገ፣ የተበተኑትን የሰበሰበ ነው፡፡

የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ‹እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይለቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ እጅጉን ይልቃል› ተብሎ እንደ ተጻፈው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ይህ ስጦታ ታላቁ ስጦታ ነው፤ በመሆኑም ይህ በዓል የክርስትና አስተምህሮ መሠረት የሆነ ታላቅ በዓል ነው፡፡ አንድ ነገር ታላቅ ስጦታ ስለሆነ ብቻ ሁላችንንም አይጠቅምም፡፡

በቤተ ልሔም ከተማ ከነበሩት እንኳን ብዙዎቹ በክርስቶስ ልደት ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ ልዩነቱ የተፈጠረው ስጦታውን በመቀበልና ባለመቀበል ነው፡፡ አብሮ በመሥራትና ባለመሥራት ነው፤ ዐውቆ በመጠቀምና ባለመጠቀም ነው፡፡ የቤተ ልሔም ሰዎች በከተማቸው የዓለምን ታሪክ የሚለውጥ ተአምር እየተሠራ መሆኑን አልተረዱም፡፡

እንኳን ታሪክ ሊሠሩ ታሪክ ሲሠራ ለማየትም አልፈቀዱም፡፡ ሌሎች ከሩቅ ሀገር ይህንን ታሪክ ለማየትና ለመስማት ሲመጡ ነው የደነገጡት፡፡ ሄሮድስም ራሱን ለመፈተሽ አልፈለገም፡፡ ሥልጣኑን በመሣሪያ ኃይል የሚያስጠብቅ መስሎት የቤተልሔም ሕጻናትን ነው ያስፈጀው፡፡

የሚገርመው ነገር የክርስቶስን መወለድ በቸልታ ያለፉት ግዴለሾቹ የቤተ ልሔም ሰዎች መከራው ግን አልቀረላቸውም፡፡ ሄሮድስ የጨረሰው የእነርሱን ልጆች ነው፡፡ መከራን በመጋፈጥ እንጂ በመተኛት ለማምለጥ አይቻልምና፡፡

ሊቃውንተ አይሁድም ዕውቀታቸውን እየጠቀሱ በመራቀቅ ጊዜውን ያለ ተሳትፎ አሳለፉት፡፡ ከተማሩት ሊቃውንት ይልቅ ያልተማሩት እረኞች ተጠቀሙ፡፡ ዛሬም እንኳን በታሪክ የምናስታውሰው እነርሱኑ ነው፡፡ የተናቁት የቤተልሔም ከብቶች ያደረጉትን አስተዋጽዖ ያህል በዳዊት ከተማ በመኖራቸው በታሪካቸው የሚመጻደቁት ቤተ ልሔማውያን አንዳች ለማድረግ አልቻሉም፡፡

የክርስቶስን መወለድ ስናስብ ሀገራችንንም እናስባት፡፡ በቤተ ልሔምና በዙሪያዋ የነበሩ ሁኔታዎች ዛሬም በሀገራችን አሉ፡፡ ቤተ ልሔማውያን በእጃቸው ያገኙትን ጸጋ መጠቀም አልቻሉም፤ በቅናት፣ በግዴለሽነት፣ በጥቅም ሽኩቻ፣ በየወገኑ በመከፋፈልና በሥልጣን ጥም ተነክረው ዕድላቸውን አባከኑት፡፡

እኛም በዘመናችን ያገኘነውን ሀገራችንን የመለወጥ፣ የማሻሻል፣ የማሳደግና የማዘመን ዕድል እንዳናጣው እንደ ልባም ሰው ማሰብ አለብን፡፡ እንደ ቤተ ልሔማውያን በቅናት ተቃጥለን፣ በግዴለሽነት ተኝተን፣በጥቅምና በሽኩቻ ተባልተን፣ በመከፋፈል ተበታትነን፣በሥልጣን ጥም ሰክረን ያገኘነውን ዕድል ከእጃችን ላይ እንዳንጥለው የምናስብበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ክርስቶስ ሁሉን ነገር ትቶ በረት ላይ እንዲተኛ ያደረገው ለእኛ ለወገኖቹ ያለው ፍቅር ነው፡፡

የሚያሰልፈው የመላእክት ሠራዊት አጥቶ አይደለም፤ በመብረቅ ማጥፋት፣ በንፍር መምታት ተስኖትም አይደለም፡፡ ፍቅር ያድናል፣ ይቅርታ ይጠግናል ብሎ እንጂ፡፡ ወገናችንን በእውነት የምንወድ ከሆነ ሰላምን እንጂ ሰይፍን ለምን እናስቀድማለን? ፍቅርን እንጂ ጠብን ለምን እንሰብካለን? አንድነትን እንጂ መለያየትን ለምን እናመርታለን? ይቅርታን እንጂ ጥላቻን ለምን እንተክላለን? ይህ በዓልኮ ሰውና መላእክት፣ ፍጡርና ፈጣሪ፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሰማይና ምድር አንድ የሆኑበት በዓል ነው፡፡

መለያየትንና መጠፋፋትን እየዘራን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ‹ሰላም በምድር ይሁን› የተባለበት ነው፡፡ የጦርነትን ዘገር እየነቀነቅን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ እረኞችና ከብቶች መጠለያ ያጣውን ጌታ ያስጠለሉበት በዓል ነው፡፡ ታድያ ዛሬ ሂድ፣… ውጣ፣…. ልቀቅ፣…. እያልን የገዛ ወገናችንን እያሳደድን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ለወገን ጥቅም ሲሉ ራስን የመስጠት በዓል ነው፡፡

ለራሳችን ጥቅም ስንል ወገኖቻችንን እያጋደልን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ሰውና መላእክት አንድ ሆነው የሰላም መዝሙር የዘመሩበት ድንቅ በአል ነው፡፡ ተለያይተን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰምን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ሰብኣ ሰገል የተወለደውን ሕጻን ለማግኘት ከሄዱበት ዐውድ ብዙውን ነገር ቀይረው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን መጽሐፍ ይናገራል፡፡

እኒያ የጥበብ ሰዎች የሰላሙን ንጉሥ ካገኙት በኋላ በሌላ መንገድ - በሌላ ኃይለ ቃል እና በሌላ እምነት የመልስ ጉዟቸውን አድርገዋል፡፡ ሲሄዱ በሄሮድስ ቤተ መንግሥት በኩል ቢሆንም ሲመለሱ ግን ጎዳናቸውን ቀይረዋል፤ ሲመጡ ‹የአይሁድ ንጉሥ የት ነው?› እያሉ ቢፈልጉትም አግኝተውት ሲመለሱ ግን ‹የዓለማት ንጉሥ› ብለው ተናግረዋል፡፡ ‹ወዴት አለ?› ብለው እየፈለጉት መጥተው ነበር፡፡

አግኝተውት ሲመለሱ ግን‹ አገኘነው› ብለው ተደስተዋል፡፡ ከእነዚያ የጥበብ መንገደኞች መካከል ኢትዮጵያውያን ዋኖቻችንም ነበሩበት፡፡ እኛ የእነርሱ ልጆችም ዛሬ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ትኅትናን፣ አብሮነትን እና መከባበርን አስቀድመን መጀመር አለብን፡፡

እንዲያ ከሆነ የነገ ተነገ ወዲያ በዓሎቻችንን ‹ሰላማችን ወዴት አለ?› በሚል ጥያቄ ሳይሆን ‹ሰላማችንን አገኘነው‹ በሚል የማረጋገጫ ቃል እንደምናከብር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እኛም ከትዕቢት ይልቅ ትኅትናን ገንዘባችን ብናደርግ ወደ ጥላቻ እና ወደ መከፋፈል ከሚወስደው መንገድ ወጥተን በሌላ የፍቅር፣ የመደመር፣ የአብሮነት እና የመተማመን ጎዳና ወደ ከፍታችን እንደምንጓዝ እምነቴ የጸና ነው፡፡

‹የመጣው እና ይመጣ ዘንድ ያለው ለውጥ በሁላችንም ጥረት የመጣ ነው› ከሚለው የባለቤትነት ስሜት ጀምሮ ‹ለሁላችንም የሚበጅ ነው› እስከሚለው የመተማመን ጫፍ ድረስ ቅን መሆን ብንችል፤ ‹የእገሌ እና የእንቶኔ ለውጥ› ከሚል መጠቋቆም ተላቀን እና እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ለሁላችንም የምትበጅ ኢትዮጵያን እንደምንገነባ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡

ፈጣሪ ሀገራችንን የምናሳድግበትንና ራሳችንንም ለታላቅነት የምናበቃበትን ዕድል ሰጥቶናል፡፡ እንደ ቤተ ልሔም ሰዎች ስንዘናጋ፣ እንደ ሄሮድስ ሾተል ስንሞርድ፣ እንደ ሊቃውንተ አይሁድ በትንሽ በትልቁ ስንጨቃጨቅ፣ እንደ ዘመኑ ሰዎች ስንከፋፈል፣ እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሥልጣንና ጥቅም ቀረብን ብለን በኩርፊያ ስናምጽ፣ ዕድሉ እንዳያልፈን፡፡

እንደ እረኞችና እንደ ሰብአ ሰገል ዐውቀን እንጠቀምበት፡፡ የሚጠበቅብንን አድርገን የሚገባንን እናግኝ፡፡ ታሪክ ማለፉ ላይቀር ወቀሳና ከሰሳን ለትውልድ አናስተላልፍ፤ እኛ በሌሎች እንደተማርነው ሁሉ፣ ሌሎችም ነገ በእኛ መማራቸው አይቀርምና፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! መልካም በዓል አመሰግናለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም