የሆሳዕና ብርሀን ወጣቶች ማህበር የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአረጋዊያን ድጋፍ አደረገ

68

ሆሳዕና  ታህሳስ 28/2011 የሆሳዕና ብርሀን ወጣቶች ማህበር ነገ የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ከአባላቱና ከተለያዩ አካላት ያሰባሰበውን 20 ሺህ ብር ለ17 አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ለገሰ፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ፍቅረአብ ደጀኔ እንደተናገረው የቆየ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነው የእርስ በርስ መረዳዳትና መደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

"አባቶቻችን በበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘወትር አቅመ ደካማና ረዳት የሌላቸውን አረጋዊያንን የመደገፍ ልምድ ነበራቸው" ያለው ፍቅረአብ፣ በአሁኑ ወቅት ይህ ነባር የመደጋገፍ ልምድ እየተዳከመ መምጣቱን ገልጿል፡፡

የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ እንደ አባቶቻችን ወገኖቻችንን መደገፍ አለብን በሚል እሳቤ 60 የማህበሩ አባላት ከራሳቸው ገንዘብ ያዋጡትንና ከተለያዩ ድርጅቶች ያሰባሰቡትን 20 ሺህ ብር ለ17 አረጋውያን በዛሬው እለት ማከፋፈላቸውን ተናግሯል፡፡

እንደ ወጣት ፍቅረአብ ገለጻ የወጣት ማህበሩ በዋናነት የተቋቋመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠትና አረጋዊያንን ለመደገፍ ነው፡፡

በሆሳዕና ከተማ ቦብቾ ቀበሌ የሚኖሩትና በወጣቶቹ ድጋፍ የተደረገላቸው ወይዘሮ በቀለች ቲዴና "ወጣቶቹ በዓልን በደስታ እንድናሳልፍ እኛን አስበው  ላደረጉልን ድጋፍ ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡

በዓል ሲደርስ ሁሌም ሀዘን ይሰማቸው እንደነበር የተናገሩት ወይዘሮ በቀለች ’’ዛሬ ልጆቼ ባደረጉልኝ ድጋፍ የገናን በዓል በደስታ ማሳለፍ እችላለሁ’’ ብለዋል፡፡

በሆሳዕና ከተማ የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አለም ደጀኔ በበኩላቸው ከአቅም ማነስ የተነሳ በዓልን በባዶ ቤት ሊያሳልፉ እንደነበር ጠቁመው ዛሬ አስታዋሽ በማግኘታቸው በዓሉን በደስታ እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል፡፡

"ለተደረገልኝ ድጋፍ ምስጋናዬ የላቀ ነው፤ እኛው የወለድናቸው ልጆች ዛሬ ሲደርሱልኝ የተሰማኝን ደስታ በቃላት መግለጽ ይከብደኛል’’ ብለዋል፡፡

የሆሳዕና ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሰሀ ታደሰ በድጋፍ ስነስርአቱ ላይ እንደገለጹት በከተማዋ በርካታ የወጣት  አደረጃጀቶች በተለያዩ የበጎ አድራጎትና የልማት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ይገኛል፡፡

የሆሳዕና ብርሀን ወጣቶች ማህበር በዚህ መልኩ አረጋዊያንን መደገፍ መቻሉ ለሌሎች ማህበራት ብቻ ሳይሆን አቅሙ ላላቸው አካላትም ጭምር ምሳሌ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ ከአባላቱና ከሌሎች አካላት ያሰባሰበውን 20 ሺህ ብር ለአረጋውያኑ እንደችግራቸው መጠን ከ1 ሺህ እስከ 1ሺህ 500 ብር ማከፋፈሉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም