በዋግ ኽምራ ለሰባት ገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

1331

ሰቆጣ ታህሳስ 28/2011 በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰባት የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የሃገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የሰቆጣ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ ማኛው እንዳሉት የኤሌክትሪክ መስመር አየተዘረጋላቸው ያሉት ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ ያልተዳረሰባቸው በደሃና፣ ዝቋላ፣ አበርገሌና ሰቆጣ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች የሚገኙ ከተሞች ናቸው።

ከእዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን አግኝተው ማሻሻያ የሚደረግላቸው ከተሞች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው አዚላ፣ አዲሱ ፍሬ፣ ሻኩራና ተለላ የገጠር ከተሞች ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎቱን የሚያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያት የተሟላ አገልግሎት ሳያገኙ የቆዩ ተላጀ፣ ድል በትግልና ዙና የገጠር ከተሞችም ማሻሻያ የሚደረግላቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“ በአዚላ፣ ተለላና ሻኩራ ገጠር ከተሞች በሚገኙ ቀበሌዎች የመስመር ዝርጋታ ሥራው በአብዛኛው የተጠናቀቀ በመሆኑ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ  አገልግሎቱን ያገኛሉ “ ብለዋል

አቶ ብታሙ እንዳሉት በተላጀ፣ ድል በትግል እና ዙና ገጠር ከተሞች እየተካሄደ ያለው የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት የመለወጥ ሥራም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል።

“ለከተሞቹ በሚደረገው የምሰሶ ለውጥ ቀደም ሲል በንፋስና ዝናብ ሲያጋጥም የነበረን የአገልገሎቱ  መቋረጥ ያስወግዳል “ ብለዋል ።

የተላጀ ቀበሌ ነዋሪ አለሜ ወዳጅ እንዳሉት የኤሌክትሪክ አገልገሎት በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ እህል ለማስፈጨት ለአምስት ሰአት በእግር ይጓዙ እንደነበር ተናግረዋል።

“የተጀመረው የመስመር ዝርጋታ ተጠናቆ አገልገሎቱ ሲጀመር ከእንግልት የሚገላግለን በመሆኑ በጉጉት እየጠበቅን ነው” ብለዋል ።

ለከተማው የተዘረጋው መስመር ተሸካሚ የእንጨት ምሰሶ በየጊዜው እየወደቀ በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ያጋጥማቸው እንደነበር የገለጹት ደግሞ የዙና ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ግርማይ አዳነ ናቸው፡፡

“ምሰሶውን ወደ ኮንክሪት የመለወጥ ሥራ ሲጠናቀቀ ከችግሩ እንላቀቃለን የሚል ተስፋ አለን” ብለዋል ።

አዲስና ማሻሻያ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በሚካሄድባቸው ገጠር ከተሞች ከ45 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል።