አትሌት ሰለሞን ባረጋ በዳይመንድ ሊግ በሁለት ማይል አሸነፈ

78
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 አትሌት ሰለሞን ባረጋ በአሜሪካ ኢውጅን ከተማ በተጀመረው ሶስተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ትናንት በሁለት ማይል አሸነፈ። ዛሬ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በአምስት ሺህ ሜትር የምትሳተፍበት ውድድር ይጠበቃል አትሌቱ ሁለት ማይል (3 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር) ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ስምንት ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ከአንድ ማይክሮ ሰከንድ ሲሆን በርቀቱም የግል ምርጥ ሰዓቱን ማስመዝገብ ችሏል። በመካከለኛና ረዥም ርቀቶች እንዲሁም በጎዳና ላይ ውድድሮች አስገራሚ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ሰለሞን የትናንት ድሉ አሁን ያለበትን ብቃት የሚያሳይ እንደሆነ መናገር ይቻላል። በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነው ፓል ቼሊሞ ስምንት ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ከ91 ማይክሮ ሰከንድ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነው ብርሃኑ ባለው ስምንት ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ከ54 ማይክሮ ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል። በውድድሩ ላይ የተካፈለው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሙክታር እድሪስ 13ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን አትሌቱ ካለው ብቃት አንጻር ውጤቱ ፍጹም ያልተጠበቀ ነው። ትናንት በተደረጉ ሌሎች ውድድሮች በ800 ሜትር ወንዶች ኬንያዊው ኢማኑኤል ኮሪር፣ በወንዶች የጦር ውርወራ ጀርመናዊው ቶማስ ሮህለርና በወንዶች የምርኩዝ ዝላይ አሜሪካዊው ሳም ሄንድሪክስ አሸናፊ መሆን ችለዋል። የዳይመንድ ሊጉ የሁለተኛ ቀን ውድድር ዛሬም ሲቀጥል 16 የውድድር አይነቶች የሚካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያውን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ውድድሮችም ይከናወናሉ። በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት ገንዘቤ ዲባባ፣ አትሌት ለተሰንበት ግደይ፣ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይና አትሌት ፋንቱ ወርቁ ይሳተፋሉ። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ዳዊት ስዩም፣ በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ሀብታም ዓለሙ ይወዳደራሉ። በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች አትሌት ተስፋዬ ድሪባና አትሌት ዳዊት ዋለ ይሳተፋሉ። አራተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም በኢጣልያ ርዕሰ መዲና ሮም ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም