የተቸገሩ ህጻናትን መደገፍ የራስን ልጅ መጻኢ ዕድል መቀየር ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

117

አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2011 በችግር ውስጥ ያሉ ህጻናትን መደገፍ የራስን ልጅ መጻኢ እድል መቀየር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት ከባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን  የዘውዲቱ መሸሻ የህፃናትና ቤተሰብ የበጎ አድራጎት ልማት ማህበርን ዛሬ በጎበኙበት ወቅት ነው።

ከጉብኝታቸው በተጨማሪ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በማህበሩ ለሚገኙ ህፃናት የአልባሳትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

በ1984ዓ.ም በእማማ ዘውዲቱ መሸሻ መስራችነት የተቋቋመው የበጎ አድራጎት ማህበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ በችግር ውስጥ ለሚገኙ 75 ህፃናት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ከእነዚህ ውስጥ ሰላሳ አምስቱ ከማዕከሉ ውጭ ከቤተሰቦቻቻው ጋር ሆነው ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት፤ "ሰላም ከሌለ ያከማቸነው ሃብት ለልጆቻችን ዋስትና ሊሆን አይችልም"።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማናችንም ልጆች ነገ ችግር ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ማሰብ እንደሚገባ አሳስበው፤ በችግር ውስጥ ያሉ ህጻናትን መደገፍ  የራስን ልጅ መጻኢ እድል እንደመቀየር መወሰድ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በገና በዓል ዋዜማ በማዕከሉ ተገኝተው ባደረጉት ጉብኝት እጅግ መደሰታቸውን የገለጹት ዶክተር አብይ፤ ህብረተሰቡ የገናን በዓል ሲያከብር ከተቸገሩ ወገኖቹ ጋር ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

እማማ ዘውዲቱ ተስፋ ሰንቀው ለበርካታ ህፃናት መጠለያና መጠጊያ መሆናቸው በኢትዮጵያ ተስፋ ያላቸው እናቶች እንዳሉ ማሳያ በመሆኑ የሳቸውን አርአያ መስፋት አለበት ብለዋል።

ዜጎች ባላቸው ሃብት እርስ በርስ መረዳዳትን እና እነዚህ ዜጎች ይህ ሀብት በጠፋ ጊዜ እንደ እማማ ዘውዲቱ ያሉ እናቶች የልጆቻቸው መጠጊያ እንደሚሆኑ አስበው ከሚተርፋቸው ማካፈል ቢችሉ መልካም ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የመረዳዳት ባህልና እሴት እየዳበረ ቢመጣም አገሪቱን መቀየር እንደሚቻል ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እማማ ዘውዲቱ የበለጠ ህፃናትን መርዳት እንዲችሉ በጎ ማድረግ የሚሹ ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

እማማ ዘውዲቱ መሸሻ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ህፃናቱን በገና ዋዜማ መጥተው ሰለጎበኟቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

ማዕከሉ በቅርቡ በደረሰበት ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ  ግማሽ ክፍሉ ላይ ሙሉ በሙሉ ውድመት ያጋጠመው ቢሆንም በተቀረው ክፍሉ አሁንም ድረስ ለህፃናቱ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም