በአማራ ክልል ከ2 ሚሊዮን በላይ አባውራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል

74

ባህርዳር ታህሳስ 28/2011 በአማራ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ አባውራዎች ቁጥር 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን መድረሱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልል ደረጃ የተዘጋጀ የማህበረሰብ ጤና መድህን ንቅናቄ መድረክ ትላንት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ በወቅቱ እንደገለፁት በክልሉ 156 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መርሀ ግብር ተግባራዊ እየተደረገ ነው ።

በዚህ አመት በቀሪዎቹ 25 የክልሉ ወረዳዎች መርሀ ግብሩን ተግባራዊ በማድረግ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን አዲስ አባዎራዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ከጥር 1 እስከ የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ አዳዲስ አባላትን የማፍራትና የነባር አባላት እድሳት ሥራ እንደሚካሄድ አመላክተዋል።

" በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አጠቃላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አባወራዎች ቁጥር ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያድጋል" ያሉት ኃላፊው አጠቃላይ የአገልግሎቱ ሽፋንም 80 በመቶ እንደሚደርስ ነው የገለጹት።

ለዕቅዱ ተግባራዊነት የፖለቲካ አመራሩን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።

"መርሀ ግብሩ ተግባራዊ እየሆነባቸው ካሉ ወረዳዎች መካከል 22ቱ የአባላት ህክምና ወጭ መሸፈን ያለመቻል ችግር የታየባቸው ናቸው" ያሉት ደግሞ በቢሮው የፈውስ ሕክምናና ተሃድሶ አገልግሎት የሥራ ሂደት መሪ አቶ አበበ ዳኘው ናቸው።

"በወረዳዎቹ በአገልግሎቱ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አለመሰራቱና ከአባላት የተሰበሰበውን ገንዘብ በወቅቱ ገቢ ያለማድረግ ለችግሩ ምክንያት ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል ።

ችግሩን ለመፍታት እያንዳንዱ ወረዳ የአባላቱን ቁጥር ከ60 በመቶ በላይ ማድረስና ከአባላት የሚሰበሰብ ክፍያን በወቅቱ ገቢ ማድረግ  እንደሚገባው አሳስበዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአባላት መዋጮ 583 ሚሊዮን ብር ገቢ  መሰብሰቡን ያስታወሱት የስራ ሂደት መሪው፣ መክፈል ለማይችሉ ከ434 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልገሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰዋል ።

"የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በመርሀ ግበሩ ትገበራ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ናቸው " ብለዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል የክልሉ መንግስት የራሱ የሆነ የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ማቋቋም መቻል አንዱ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አስተዳዳሪ ሲስተር ክሽን ወልዴ በበኩላቸው በወረዳው ባለፉት ሦስት ዓመታት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው ከአጠቃላይ አባወራዎች  ግማሽዎቹ በአባልነት ተመዝግበው  በጎንደር ሆሰፒታልና በሌሎች ጤና ተቋማት አገልግሎቱን እያገኙ መሆናቸውን ሲስተር ክሽን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም