የባዕኸር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት እጥረት ምክንያት መዘግየቱ ተገለጸ

1155

መቀሌ  ታህሳስ 28/2011 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን እየተገነባ ያለው የባዕኸር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት እጥረት  ከተያዘለት ጊዜ በላይ መዘግየቱ ተገለጸ።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ያለበት ደረጃን አስመልክቶ በትግራይ ክልልና በፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች ትናንት መግለጫ ተሰጥቷል።

የትግራይ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ አስኪያጅ አቶ አንገሶም ገብረመስቀል እንዳሉት የባዕኸር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በፌዴራል መንግስት በጀት ድጎማ በአራት ክልሎች ከሚገነቡ አራት ፓርኮች መካከል አንዱ ነው።

ለፓርኩ ከተሰጠው አንድ ሺህ ሄክታር መሬት በመጀመሪያው ምዕራፍ በ250 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ሥራ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር  ላይ መጀመሩን ገልጸዋል።

በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ግንባታው የተጀመረው ፓርክ  በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ቢታቀድም እስካሁን ደረስ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ በዕቅዱ መሰረት በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም እስካሁን ከአጠቃላይ ስራው ከ33 በመቶ በላይ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለግንባታው መጓተት ዋና ምክንያት የበጀት እጥረት መሆኑንም አቶ አንገሶም ተናግረዋል፡፡

አስካሁን ድረስ በፖርኩ ግንባታ ሥራ የዘጠኝ ጥልቅ ውሀ ጉድጋድ ቁፋሮ፣ በፓርኩ ውስጥ ለሚኖሩ ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት፣ የአስተዳደር ህንጻ እንዲሁም የስልጠና ማዕከል በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ አንገሶም እንዳሉት የፓርኩ ግንባታ የተጀመረው የማሽላና የሰሊጥ እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅኦና ማርን በመቀነባበር ወደ ውጭ ለማቅረብ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡

የባዕኸር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን እስከ ሰኔ ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ አንገሶም አመልክተዋል።

አግሮ ኢንዱስቱሪው ፓርኩ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ምርት ስራ ሲሸጋገር እስከ 200 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የሥራ እድል ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ አንገሶም ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አንገሶም ገለጻ ለፓርኩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ የዲዛይን ሥራና ሌሎች ስራዎች በሂደት ላይ ይገኛሉ።

የኢፌድሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መብራህቱ መለስ በበኩላቸው አገሪቱ ግብርና መር ኢኮኖሚውን ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር ታስቦ በአራት ክልሎች የአግሮ ኢንዱስተሪ ፓርኮች እንዲገነቡ መንግስት ቀደም ሲል መወሰኑን አስታውሰዋል።

በዚህ መሰረት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች በተመረጡ ቦታዎች በመጀመሪያው ምዕራፍ አራት አግሮ ኢንዱስቱሪ ፓርኮች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

“ለአራቱ አግሮ ኢንዱስቱሪ ፓርኮች የተያዘው በጀት ፕሮጀክቱ በሚጠይቀው ወጪ ሳይሆን በህዝብ ብዛት ቀመር መሆኑ ለግንባታው መጓተት ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል፡፡

በእዚህም በወቅቱ አሰራሩ ትልቅ ስህተት እንደነበረበት ነው የገለጹት፡፡

በበጀት አመዳደቡ ለተፈጠረው ስህተት ኤጀንሲው ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ዶክተር መብራህቱ ተናግረዋል፡፡

የባእኸር አግሮ ኢንዱስቱሪ ፓርክን ግንባታ ሥራ እያከናወነ ያለው ሱር ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህብር ፕሮጀክት ሥራ እስኪያጅ አቶ መሐመድአብዱ አሕመድ ፕሮጀክቱ ከተያዘለት ጊዜ ገደብ መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡

በመንግስት የፋይናንስ እቅርቦት እጥርት ምክንያት ፕሮጀክቱ መጓተቱንና በእዚህም ለተጨማሪ ኪሳራ እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ተቋራጩ ላከናወነው ሥራ ከፌደራል መንግስት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ድርጅቱ እንዳልተከፈለው በማሳያነት ገልጸዋል፡፡

የመንግስት የፋይናንስ አቅርቦት ከተሻሻለ እስከበጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ግንባታውን ማጠናቀቅ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡