የትግራይ ክልል ዓመታዊ የብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር ቀጥሏል

66

መቀሌ ታህሳስ 28/2011 የትግራይ ክልል የ2011 ዓመታዊ የብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር እንደቀጠለ ነው።

በተለያዩ አይነቶችና ርቀቶች በስድስት ቡድኖች መካከል እየተካሄደ ባለው ውድድር ከ100 በላይ ብስክሌተኞች እየተሳተፉ መሆኑን የክልሉ ብስክሌት ፌደሬሽን አልቢትር ጸሐየ አደም ለኢዜአ ተናግረዋል።

በመቀሌ ከተማ ትላንት በተካሄደ 40 ኪሎ ሜትር የወንዶች የማውንቴን ውድድር ከመቀሌ የመጠጥ ወሃ አገልግሎት ይተባረክ ታጀበ አንደኛ በመውጣት አጠናቋል።

ከሙሉ ብርሃን ፕሮጀክት ዮናታን አታክልቲ እንዲሁም ከደስታ አልኮልና መጠጥ አፍሬም መዓርግ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ውድድሩን ጨርሰዋል።

በቡድን ደግሞ ደስታ አልኮልና መጠጥ፣ መቀሌ መጠጥ ውሃ አገልግሎትና ሙሉ ብርሃን ፕሮጀክት እንደየ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በሴቶች የማውንቴን ብስክሌት ውድድር "መቀሌ 70 እንደርታ ክለብ" ን ወክለው የቀረቡ እዩኤል ካህሳይ፣ ሜላት ዮሐንስና ክንድሃፍቲ መረሳ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ መያዝ ችለዋል።

በተመሳሳይ የሴቶች የቡድን ውድድር መቀሌ 70 እንደርታና ሙሉ ብርሃን ፕሮጀክት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን ማጠናቀቃቸውን አልቢትር ፀሐየ አደም ገልጸዋል፡፡

በማውንቴን ብስክሌት በ "ቢ" ኮርስ የወንዶች ውድድር ከጉና ከሮን ታደሰ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በግል የቀረበው ኤርትራዊው ሳልማን ሳሊህ ሁለተኛ እንዲሁም ከጉና ነጋሲ ኪዳነማርያም ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በተመሳሳይ የወንዶች የቡድን ውድድር የክለቦች ውጤት ጉና፣ ብሩህ ተስፋ የመስኖና ቴክኖሎጂ ስራዎችና፣ ወልዋሎ አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።

በ"ኤ" ኮርስ ብስክሌት ከመቀሌ-አጉላዕ ዴስአ 110 ኪሎ ሜትር ደርሶ መልስ ውድድር ከትላንት በስቲያ የተጀመረው የክልሉ የ2011 የብስክሌት ሻምፒዮና የፊታችን ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ከወጣው መርሀ ግብር ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም