በጉጂ ዞን የደረሰ ሰብልን ከብልሽት ለመከላከል በደቦ እየተሰበሰበ ነው

54

ነገሌ ታህሳስ 28/2011 በጉጂ ዞን እየጣለ ባለው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብልሽት ናብክነት ለመከላከል በደቦ የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ ነው፡፡

የዞኑ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት እንደገለጸው በአካባቢው በመኸሩ ወቅቱ 115 ሺህ ሔክታር መሬት ገብስ፣ ባቄላ፣  ስንዴ ፣ በቆሎና ጤፍ  በመሳሰሉት ዋና ዋና ሰብሎች ለምቷል ።

በተለይ  በቦሬ ዳማ ፣ አናሶራና ሀሮ ወላቡ ወረዳዎች እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ  በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡

ከብክነትና ብልሽት ለመከላከል 603 የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በቅርበት አርሶ አደሩን እንዲደግፉ በማድረግ ምርቱን በደቦ ለመሰበሰብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ታደሰ ብዙነህ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ቀደም ሲልም ለ15 ሺህ አርሶ አደሮች በመኽር አዝመራ አሰባሰብ ላይ ያተኮረ የአጭር ጊዜ ስልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

አርሶ አደሩ የልማት ጣቢያ ሰራተኞቹን ምክርና ድጋፍ በመቀበል የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የሚደርስ የምርት ብክነትን እንዲከላከል መክረዋል፡፡

በመኽሩ አዝመራ ከተሳተፉ 61 ሺ 200 አርሶ አደሮች መካከል 4 ሺህ ሴቶች ሲሆኑ እስካሁን ከለማው  መሬት ከግማሽ በላይ  መሰብሰቡን አስረድተዋል።

በዞኑ ቦሬ ወረዳ የጉቱ ሬጂ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጂሎ ዱከሌ በሰጡት አስተያየት በመኽር ወቅት በ4 ሄክታር  መሬት ላይ ያለሙትን የገብስና  የስንዴ  ምርት ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን እየሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አልፎ አልፎ ወቅቱን ሳይጠብቅ እየጣለ ያለው ዝናብ እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልፀው ተፈጥሯዊ ችግሩን በዘዴ ለማለፍ ከልማት ጣቢያ ሰራተኞች   ያገኙትን ምከር በመጠቀም  የደረሱ ሰብሎችን በደቦ መሰብሰቡን  እንደቀጠሉ  ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደር ገመዳ ጎቡ በበኩላቸው በመኽር አዝመራ በተለያዩ ሰብሎች ካለሙት መሬት እስከ 48 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

"የምርት ብክነትና ብልሽት ለመከላከል ሰብልን በዘዴና በወቅቱ እንዲሰበሰብ በልማት ጣቢያ ሰራተኞች እየተሰጠ ያለው ትምህርት ተጠቅሜ አቅሜን የቻለው ሁሉ እያደረግኩኝ ነው" ብለዋል ።

በዞኑ በመሰብሰብ ላይ ካለው የመኽር አዝመራ ሁለት ሚሊዮን 900ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም