ትረስት ፈንድ ላይ መተማመን ለመፍጠር ጠንካራ ስራ መሰራት አለበት-የዲያስፖራ አባላት

80

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2011 የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ላይ ይበልጥ መተማመን ለመፍጠር ጠንካራ ስራ መሰራት አለበት ሲሉ አንዳንድ የዲያስፖራ አባላት ተናገሩ።

የዲያስፖራ ማህበር በበኩሉ ከትረስት ፈንዱ ምክር ቤት ጋር ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በቀን አንድ ዶላር አስተዋፅዖ በማድረግ ለወገናቸው የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድን አቋቁመው ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

የሚሰበሰበው ገንዘብም ለመሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች ልማት እንደሚውል የተገለጸ ሲሆን እስከተያዘው ወር መጀመሪያ ድረስ በሚፈለገው ልክ ገቢ እየሆነ አልነበረም።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ዲያስፖራዎች እንዳሉት የዶክተር አቢይ የለውጥ ጉዞ በአብዛኛው ዲያስፖራ ላይ እምነት የጣለ ቢሆንም ቀደም ሲል የነበሩ እምነት ማጣቶች ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፉም።

በአሜሪካ ቺካጎ ሃርፐር ኮሌጅ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ መዋጮ 365 ዶላር ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸው የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን በቂ አለመሆኑንና በዚህም ማዘናቸውን አልሸሸጉም።

ገንዘቡ በሚፈለገው ልክ ላለመሰብሰቡ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን መፈተሽ እንደሚገባ ጠቁመው ምክር ቤቱም ወደ ህብረተሰቡ ቀርቦ ቅስቀሳ ማድረግና ተፅዕኖ መፍጠር አለበት ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ይሰራሉ ተብለው የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የሚፈጥሩት ተጽዕኖ መኖሩን የሚናገሩት ደግሞ የአሜሪካ ሚኔሶታ ነዋሪ ወይዘሪት እፀገነት ኃይሉ ናቸው።

ከመገናኛ ብዙሃን ጀምሮ የትረስት ፈንዱ ምክር ቤትም ቋሚ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሚናገሩት ዲያስፖራዎቹ በቀጣይ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የገንዘብ አሰባሰቡን የሚደግፉ ልዩ ልዩ የአሰባሰብ ስርዓቶች ሊፈጠሩ ይገባል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው የትረስት ፈንድ ምክር ቤቱ ቋሚ መገኛ ስለሌለው ዲያስፖራው ስለትረስት ፈንዱና ስለሚሰሩ ፕሮጀክቶች ጥያቄዎችን ለማህበሩ እንደሚያነሳ ገልፀዋል።

ጥያቄውን ለመመለስም ማህበሩ ከምክር ቤቱ ጋር በጋር ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

አስተያየት ከሰጡት ዲያስፖራዎች መካከል ከፊሉ በዓላማው ብናምንም በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን አስተዋጽኦ ማድረግ አልጀመርንም ያሉ ሲሆን በቀጣይ ለመሳተፍ ቃል ገብተዋል። የጀመሩትን ደግሞ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ በተጠበቀው ልክ አለመሆኑንና ዲያስፖራውም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ዳግም ጥሪ ካቀረቡ በኋላ የፈረንጆቹ አዲስ አመት ሳይገባ ከታሰበው አንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

እስከዛሬዋ ዕለት ድረስም ከ12 ሺህ በላይ በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ዲያስፖራዎች ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።

ከ240 ሺህ ዶላር በላይ በመለገስ የአሜሪካዋ ሜሪላንድ ግዛት ዲያስፖራዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም