ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው ባህርዳር ከነማን 2 ለ 1 አሸነፈ

94

ድሬዳዋ ታህሳስ 27/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሣምንት ጨዋታ ድሬዳዋ  ከነማ  በሜዳው  ባህዳር ከነማን 2 ለ 1 አሸነፈ፤

በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የሁለቱ ቡድኖች ድጋፊዎች የታጀበው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የኳስ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ወደ ጎል በመቅረብና ሙከራ በማድረግ ድሬ ከነማ የተሻለ ነበር፡፡

ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገው ሀብታሙ ወልዴ በ29ኛው ደቂቃ ለድሬ ከነማ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጠሮ ቡድኑ እንዲመራ አደረገ፤ በ41ኛው ደቂቃ ደግሞ ኢተሞና ኬሙና ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላቱ በመግጨት ሁለተኛውን ጎል ለድሬዳዋ ለከነማ አስቆጠሮ ለእረፍት ወጥተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽም ድሬዳዋ ከነማዎች የተሻለ የተጫወቱ ሲሆን በርካታ ያለቀላቸው ጎሎችን ስተዋል፡፡

ጨዋታው ማጠናቀቂያ ላይ ባህር ዳር ከነማዎች ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት ፍቃዱ ደነቀ ወደ ጎል ቢቀይረውም ከሽንፈት አላዳናቸውም፡፡

የድሬዳዋ ጊዜያዊ ዋና ማሰልጠኛ ስምኦን አባይ “ተጋጣሚያችን የደረጀና ጠንካራ ቡድን ነው፤ ነገር ግን ዛሬ ቡድናችን ከሌላው ጊዜ የተሻለ ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወቱ አሸንፈናል” ብለዋል፡፡

“ጎል ማስገባት ላይ ክፍተት አለ ፤በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ጎል የሚሆኑ ኳሶችን ስተናል ለቀጣይ ጨዋታ የተጫዋቾቻችን ስነ-ልቦና የተሻለ መተማመን እንዲፈጠር እሰራለሁ” ብለዋል፡፡

የባህር ዳር ከነማ ዋና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በበኩላቸው “እስከዛሬ ካደረግናቸው ጨዋታዎች የዛሬው የደከመና የወረደ ጨዋታ ነው የተጫወትነው” ብለዋል፡፡

“አራት ተጫዋቾቼ በጉዳት በቡድኔ ውስጥ ባለመኖራቸው ዋጋ አስከፍሎናል፤ተጋጣሚያችን ብልጫ ወስዶ አሸንፎናል” ነው ያሉት ፡፡

“የድሬዳዋም ሆኑ ረጅም ርቀት አቋርጠው የመጡት ደጋፊዎቻችን ላሰዩት ከፍተኛ ስፖርታዊ  ጨዋነትና ፍቅር አመሰግናለሁ”ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም