አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ዜጎች ይቅርታ ተደረገላቸው

92
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው ማረሚያ ቤት የሚገኙ ዜጎች ከእስር እንዲፈቱ ተወሰነ፡፡ እንዲፈቱ ከተወሰነው ታሳሪዎች መካከል ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከየመን ሰነዓ በቁጥጥር ሥር ውለው ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በልዩ ሁኔታ ይቅርታ እንደተደረገላቸው ተገልጿል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ አቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩ 27 ግለሰቦችና አራት ድርጅቶች ክስ እንዲቋረጥ ተወስኗል። በተጨማሪም በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የተፈረደባቸው 576 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ፤ በሽብር ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው በሒደት ላይ ያለ 137 ዜጎች ደግሞ ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ነው የገለጹት። በአሁኑ ወቅት የተካሔደው የይቅርታና የክስ ማቋረጥ ሒደት መንግስት በሕብረተሰቡ ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሳውን የፍትሕ ዘርፍ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመፍታትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል። እነዚሁ በይቅርታ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ተከሳሾች በእስር ጊዜያቸው ባሳዩት ስነ-ምግባር፣ መፀፀትና ከማረሚያ ቤት ቢወጡ ለሕብረተሰቡና ለራሳቸው ደሕንነት የማያሰጉ መሆናቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት። በወንጀል ሕግ ተከሰው ክሳቸው ተቋርጦ በይቅርታ እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው 576 ታሳሪዎች መካከል 18ቱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም