የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

85

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2011 የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድከር ከመጪው ማክሰኞ ጀምሮ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ከታህሳስ 30 እስከ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚቆይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሊዮ ቫራድከር በቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ታውቋል።

አየርላንድ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የኢኮኖሚ ፣ ፖለቲካ ፣ ማህበራዊ ለውጦች ከሚደግፉ የአውሮፓ አገራት ግንባር ቀደም ስትሆን ፣ በአይሪሽ የልማት ተራድኦ አማካኝነት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ፕሮጀክቶችን እንደምትደግፍ ተገልጿል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ለምታደርገው እንቅስቃሴም ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች።

ሁለቱ አገራት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ አየርላንድ በ1986 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ስትከፍት፤ ኢትዮጵያም በአየርላንድ ደብሊን 1995 ዓ.ም ኤምባሲዋን ከፍታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም