በትግራይ ክልል ዘንድሮ በ70 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል

921

መቀሌ ታህሳስ 27/2011 በትግራይ ክልል ዘንድሮ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ግድቦችን ከደለል መከላከልና የከርሰ ምድር ውሃን ማጎልበት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዳሬክተር አቶ ክፍሎም አባዲ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው የበጋ ወቅት በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ70 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይካሄዳል፡፡

በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ በ50 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄደው ስራ የከርሰ ምድር ውሃን ለማጎልበት በሚያግዝ መልኩ ይከናወናል፡፡

በቀሪው 20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ የተከዜ ሃይል ማመንጫ ግድብን ከደለል መከላከል በሚያስችል  ስራ ላይ በማተኮር ይሰራል፡፡

በዚህም ከ1 ሺህ 400 በላይ በሚሆኑ ተፋሰሶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ስራው በመጭው  ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ ለ20 ተከታታይ ቀናት ይከናወናል፡፡

በልማቱም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ህዝብ በነፃ ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በስራው የሚሳተፈውን ህዝብና ዝርዝር  ስራዎችን በዘመናዊ የመረጃ ስርዓት የማስፈር ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ክፍሎም “ይሄም  ለቀጣዩ ትውልድ ተጨባጭ እውነታን ለማስረከብ የሚያግዝ ነው” ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ዓድዋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተስፋሚካኤል ትኩዕ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የሚያስገኘውን ጥቅም በተግባር ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ለ20 ቀናት ነጻ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ካሉት ሶስት ከፍተኛ ተፋሰሶች መካከል እስከ 75 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው የተከዜ ተፋሰስ መሆኑን በቅርቡ የክልሉ መንግስት ያካሄደው ጥናት አረጋግጧል፡፡